Monday, September 14, 2015

ዊንታና ሀበን

ዊንታና ሀበን
ቃልኪዳን ኃይሉ
(ከ ለምን አትቆጣም?መጻሕፍ የተወሰደ)
ዊንታና ሀበን የልጅንት ወዳጆቼ ናቸው፡፡ ዊንታ እኩያዬ ስትሆን ሀበንን ደግሞ እኔ በሁለት አመት እበልጣታለሁ፡፡ ዊንታና ሀበን ቆንጆዎች ናቸው፡፡ የቁንጅናና ውበት አድናቂ እንዲሁም ጎበዝ መራጭ እንደሆንኩ ያወኩት አሁን አድጌ በሃያ አራት አመቴ ምስላቸውን ስመለከት ነው፡፡
እኔ የምወዳት ሀበን ቁርጥ እናቷን ነች፡፡ ስንደዶ የመሰለ አፍንጫ አላት፤ ክብ እና ትንሽ ፊቷ ላይ በየትኛው ፊቷ ተሸክማ ምን ልታይበት እንደሆነ ባላውቅም አሎሎ የመሰለ ጥርት ያለና ነጭ ዓይን አላት፡፡ ቀይ ነች፡፡ ስትስቅ የዓለም ምስጢር በሙሉ ፈገግታዋ ውስጥ እንዳለ ሁሉ አልያ አንዳች ቅኔ ይዘረፍ ይመስል ያያትን ታፈዛለች፤ ያልታወቀ አዲስ ግኝት የሚያወጣ ይመስል ከንፈሯ ለፈገግታ ቦታውን ሲለቅ ፈዞ ማየት ግድ ነው፤ ተፈጥሮ ውበትን ተጠቅሞ ሀበንን እንድናይ ያስገድደናል፡፡ ከምንም በላይ ግን ያኔ በስድስት ብር የሚገዛው ሰማያዊውና ነጭ ነጠላ ጫማዋ ላይ የሚያርፉት ውብ እግሮቿ ይገዙኛል፡፡ ለብቻቸው ዓይን፣ ከንፈርና ነጭ የሚፍለቀለቅ ጥርስ ያላቸው ይመስለኛል፡፡ ሳየቸው ያፈዙኛል፡፡ እቺ ከላይም ከታችም ቆንጆ የሆነችው የኔ የምላት ሀበን ውበት ነው፡፡ ዊንታ አሁን ከገለፅኩት ውበት ሳንቀንስ ሳንጨምር ጠይም ነች፡፡ ሀበን ግን ቀይ ነች የኔ ደመ ሙሉ፡፡
የነ ዊንታና ሀበን ቤት ከእኛ ቤት በስተቀኝ በኩል ይገኛል፡፡ እነሱ ቤት ሲንኳኳ እኛ ቤት ይሰማል፤ የነ ዊንታና ሀበን ቤት ቅቤ ሲነጠር እኛ ቤት ይሸታል፤ እኛ ቤት በርበሬ ሲደለዝ እነ ሀበንን ያስነጥሳቸዋል፤ እነ ዊንታና ሀበን ቤት የተሰራው ክሽን ያለ የሽሮ ወጥ ሽታ እኛ ቤት ምሳ ሰአት መድረሱን ያበስረናል፤ የኔ እናት እቤት ከሌለች ችግር የለም የነ ዊንታና ሀበን እናት አለችልኝ፤ እነ ዊንታና ሀበን የሌላ ሰፈር ልጅ ቢጣላቸው ችግር የለም እኔ አለሁላቸው ብፈነከትም ልፈንከት እነ ዊንታና ሀበን አይደሉ እጣላለሁ፤ በጉልበት ቢበልጠኝም ከመፈነካከት ወደ ኋላ ብዬ አላውቅም፡፡ ለነ ዊንታና ሀበን ብዬ ተጣልቼ ግን ብዙ ተጎድቼ አላውቅም ሳላውቀው እንደ አንበሳ በሙሉ ልቤ ስለምጎፈላ ልጆች ይፈሩኝ ነበር፡፡
ፍቅር ያዘዘው ልብ አይፈራም፤ ሺ ጎልያድ ቢመጣ ልብ ያለው አንድ ዳዊት በአንዲት ጠጠር ይጥላል፡፡ ጉልበት ከልብ ነው ለካ፤ ምንም ያህል ቢጠነከር፤ ተፈጥሮ የአካል ጉልበትን ብትሰጥ ልብ ሊያምንበት ግድ ነው፤ ልብ ከፈቀደ አእምሮ መላ አካልን ያዛልም ይታዘዛልም፤ ያኔ ነው ለጥንካሬና ለማሸነፍ የሰባ ሰውነት ሳይሆን ያመነ ልብ እንደሚያስፈልግ የገባኝ፡፡
እኛ እንዲህ ነው ያደግነው፡፡ እኛ ቤት አኩኩሉ እየተቆጠረ እነ ዊንታና ሀበን ቤት ተደብቀናል፤ እኛ ቤት እንጀራ ሳይጋገር ቀርቶ እኔን እርቦኛ አያውቅም የዊንታና ሀበን እናት አብልታኛለች፤ እነ ዊንታና ሀበን ቤት ወጥ ሳይሰራ ቀርቶ የኔ እናት የዊንታና ሀበንን እጆች አስታጥባ ምሳ በራሷ እጅ እያጎረሰች አብልታቸዋለች፡፡ ከነ ዊንታና ሀበን ጋ ተኳርፈን እናቴ አስታርቃን ከዚያ ለሁላችንም ጠጠር ከረሜላ ገዝታልናለች፡፡ የዊንታ እናትም ከገበያ ቀይ እና ነጩን ዱላ ከረሜላ ለሁላችንም ገዝተውልን አምጥተው ሰጠውናል፡፡ እንዲህ እያልን ነው እኔ ዊንታና ሀበን ያደግነው፡፡
ከአባሮሽ፣ ከድብብቆሽ፣ ከሌባና ፖሊስ፣ መዝሙር ከመዘመር ሌላ የነ ሀበን አባት በገዙልን ሁሌም ንፉኝ በሚለው ነጭ እና ጥቁር ካፖርተኒ ኳስ እንጫወት ነበር፡፡ ድሮ ስንጫወት አንድ ጎል አለ ሶስታችንም እንፋጠር እና ጎል እናገባ ነበር፡፡ ጎል ያገባውም ሰውም ጎበዝ አሸናፊ ይባላል፡፡ እንዲህ ነበር የእኛ ኳስ ጨዋታ፡፡ ግን ከጊዜ በኋላ ዊንታና ሀበን አጨዋወታቸውን ቀየሩ፡፡ “እኛ ኤርትራ ነን አንተ ኢትዮጵያ ሆነህ እንጫወት” ይሉኝ ጀመር፡፡
“ኤርትራ እኮ ክፍለ ሀገር አይደለችም እንዴ? አታንስባችሁም? ኢትዮጵያ ደግሞ ሀገር ነች ስለዚህ እኔ እኮ እበልጣችኋለሁ” እላቸዋለሁ እነሱ ግን “አይ ባባ ኤርትራ ራሷን የቻለች ሀገር ነች ብሎናል እኛ እሷን ወክለን ነው የምንጫወተው” ይሉኝ ጀመር፡፡
ለካ ጦርነት ቤተሰብ ውስጥ ነው የሚሰራው፡፡ ለካ ልጅነት የሚቀረፀው በእናትና አባት ነው፤ በልጆች አእምሮ ምንም መዝራት ይቻላል፤ ፍቅርም ሆነ ጥላቻ ልጆች የተሰጣቸውን ይቀበላሉ፡፡ አሁን አሁን ሀገር አስተዳዳሪዎች በክፋት ሲነቅዙ፤ በተንኮል ሲጠላለፉ፤ ማስተዳደር ትተው ሲገዙ፤ በቀናነት መምራት ትተወ ህዝብን የመከራ ቀንበር ሲያሸክሙ፤ ታላቅ ያደርጉናል ስንል አንሰው ሲያሳንሱን ሳይ ብዙም አይገርመኝም፡፡ ይህ የወጡበት ማህበረሰብ ውጤት ነው፡፡ ከራሳቸው ምቾት ይልቅ የሌላው ደስታ የሚያበሳጫቸው ወላጆች ያነጻቸው፤ ያሳደጋቸው ቤተሰብ እንዲህ እራሱን በተንኮልና ጥላቻ ያነቀዘ ነው፤ ምቀኝነት ትንሽነት ከላዩ ላይ የተጣቡት ቤተሰብ ያፈራቸው እንደሆነ ይሰማኛል፡፡ ስለዚህ እነዚህ ሰዎች መቼም መቀየር አይችሉም፡፡ ማህበረሰቡ በክፋት ሰብሯቸው እነሱ ራሳቸውን በበጎ ማቅናት ይከብደቻዋል፤ ቢቻል እንኳ የበዛው ክፋት፣ ተንኮል፣ ምቀኝነት፣ ሸር… ይጎትታቸዋል፡፡
ዊንታና ሀበንም ተቀየሩ እኔም ልጅ ስለነበርኩ የማላውቃትን ኤርትራ እንዳስብ ተገደድኩ፤ እነሱ ኤርትራ ነን ሲሉ እኔም ኤርትራ ምን ብትሆን ነው ብዬ ማብሰልሰል ጀመርኩ፤ የልጅነት ጓደኞቼን ልብ ያሸፈተችው ኤርትራን ማንነት ለማወቅ መጣጣር ጀመርኩ፡፡ ኤርትራ ሳትሆን ጎረምሳ ልጆቿ በኢትዮጵያ ቀኝ ተገዝተናል እንደሚሉ ሰማሁ፡፡ ግራ ገባኝ ኢትዮጵያ የኔ፣ የዊንታና ሀበን ሀገር ቀኝ ግዛትን አብዝታ የምትጠላ አይደለችም እንዴ? እንዴት ሌላውን ቀኝ ትገዘለች እያልኩ ማብሰልሰል ያዝኩ፡፡ እናቴን ጠየኳት ወሬ ነው አለችኝ “ኢትዮጵያ ማንንም ቀኝ ገዝታ አታውቅም፡፡ ይልቁንስ ሌሎች የአፍሪካ ሀገራት ነጻነታቸውን እንዲያገኙ የጣረች ብሎም ዋጋ የከፈለች ነች፡፡ ለዚህም ነው ብዙ የአፍሪካ ሀገሮች የኢትዮያን ባንዲራ የመሰለ ለራሳቸውም የሚያደርጉት” አለችኝ እናቴ በኩራት፡፡ ይህንን ስሰማ ደስ አለኝ፡፡
ታዲያ የኤርትራ አንዳንድ አግድም አደግ ጎረምሶች ኢትዮጵያ ቀኝ ገዝታናለች የሚሉት ለምንድነው? እያልኩ ማሰብ ጀመርኩ፡፡ በጊዜው መልሱን ባላገኘውም አድጌ ግን መልሱን አውቄዋለሁ፡፡ ለካ ነገሩ እንዲህ ነው ዓለም የጥቂቶችን አናሳ ጥያቄ የሚሰማበት ጆሮ የለውም፤ ስለዚህ ሀሳቡ የአንድ ሰውም ቢሆን ሲጠየቅ ግን ሁሉ አሉ፤ ሁሉ ፈለጉ ተብሎ ነው፡፡ የኔ ሳይሆን የኛ ጥያቄ ተብሎ ነው፤ መረረኝ ከፋኝ ሳይሆን የሚባለው ሁላችንንም አማራችሁናል አስከፍታችሁናል ነው የሚባለው፡፡ የብዙዎች ተወካይ አንድ ሰው ሊሆን ይችላል፡፡ ያ አንድ ሰው የራሱን አላማ ለማስፈጸም የብዙዎች ድምጽ ያስፈልገዋል፡፡ የብዙዎችን ድምጽ ካገኛ በኋላ ግን የራሱን አላማ ያስፈጽማል እንጂ ለብዙዎች አይቆምም፡፡ በሁሉ ድጋፍ የመጣው ለብቻው ይሆናል፤ ለራሱና ለጥቂት ወዳጆቹ ይጥራል፡፡ የትም ይሁን የት ፖለቲካ እንዲህ ነው፡፡ በብዙ ስም ይመጣና፤ ለብዙዎች እሞታለሁ ይባልና፤ በተቃራኒው ብዙዎችን ገሎና መስዋእት አድርጎ ለራስ መኖር ጀመራል፡፡
አዲስ አበባ ተወልደው ኢትዮጵያ አድገው ኤርትራዊ መሆን የፈለጉት የልጅነት ጓደኞቼ ጉዳይ ግራ እየገባኝ መጣ፡፡ ካደጉባት ኢትዮጵያ ይልቅ የማያውቋት ኤርትራ ትናፍቃቸው ጀመር፡፡ ከኔ የልጅንት ጓደኛቸው ይልቅ የማያውቋቸው የኤርትራ ጉብሎች በአይነ ህሊናቸው ይታዩዋቸው ጀመር፡፡ አላዝንባቸውም ምክንያቱም እንዲህ ያለውን ድውይ አስተሳሰብ ያሰረፀባቸው ማን እንደሆነ ስለማውቅ፡፡
ዘመኑ ነው፡፡ ዘመን እኮ በመሪዎች ይሰራል፡፡ መልካሙም ሆነ ክፉው ዘመን በመሪዎች አስተሳሰብ ይቃኛል፡፡ ልጅ ሆኜ እናቴ ስትነግረኝ “ድሮ ድሮ ትልቅ ሀገር ነበርን፤ ሱዳንና ሶማሌን ጨምሮ እስከ የመን እንገዛ ነበር እኛ ኢትዮጵያውያን” ብላኛለች፡፡ ያ ዘመን መልካሙ መሪ በነበረበት ጊዜ ነው፡፡ አሁን ደግሞ ህፃናት እንኳ የሚሳቀቁባት ሀገር፤ ልጆች ከጨዋታ ዘለው ስለሀገር መቆረስ እረፍት አጥተው የሚጨነቁባት ሆናለች፡፡ የልጅነት ጓደኞቻችን ሀገር ጥለው ይሄዳሉ? አይሄዱም? ብለው የሚረበሹበት ዘመን፡፡ ቅድም ብያለሁ ዘመንን መሪዎች ይዋጁታል፡፡
ነጋሪት ተመታ አዋጅ ተነገረ “ኤርትራውያን ወደ ሀገራችሁ” የሚል፡፡ ሁላችንም ደነገጥን የነ ዊንታና ሀበን ሀገር እዚህ ነው፡፡ ሰፈራቸው እኛ ሰፈር ነው፡፡ ኤርትራ እኮ ሰፈር የላቸውም፤ ሄደው ያፈሩ እንደሆ እንጂ አንድም ጓደኛ የላቸውም፤ የነ ሀበን ጓደኛ እኔ ነኝ፤ የነ ዊንታ ጎረቤት እኛ ና ሌሎች የሰፈራችን ሰዎች ናቸው፤ እነ ዊንታ የትም አይሄዱም፤ ምንስ መሄጃ አላቸው፤ መሄጃቸው የኛ ቤት ነበር፤ ጠባቂያቸው እኔ ነበርኩ ከጠላት ተከላክዬ የምደባደብላቸው፡፡
ቁርጡ ቀን ሲመጣ እነ ዊንታም ሆኑ ቤተሰቦቻቸው ደነገጡ፤ እንደ ቀልድ የታየው መገንጠል የሚሉት ጣጣ ለካ ብዙ መዘዝ አለው፡፡ ተወልደው ያደጉበትን፤ ውሃ ተራጭተው አፈር ፈጭተው የለመዱትን ሰፈር፤ በሰርግ ጨፍረው በለቅሶ አዝነው አስተሳዝነው የኖሩበትን፤ የታመመ አስታመው ቢታመሙ ቀኑን ሙሉ “በጎ ሆንሽ?” የሚልን ጎረቤት እንደ ቀልድ ማጣት፤ ከድህነት ተነስተው ሀብት ያፈሩበትን ምድር እንዲሁ ከመሬት ተነስተው ደህና ሁኚ ብሎ መውጣት ይከብዳል፡፡ ሀገር ማለት መሬቱ አፈሩ አይደለም ለካ፡፡ ሰላምታው፣ ፍቅሩ፣ ሀዘኑ፣ ለቅሶው፣ ሰርጉ፣ አውዳመቱ፣ እድሩ፣ ሽምግልናው፣ ልምዱና መላመዱ… ወዘተ ነው ሀገር ማለት፡፡ ሀገር ማለት አፈር ቢሆንማ ኤርትራም እኮ የኢትዮጵያ ነች፤ ብዙም ከጎጃም ወይም ከጋሞ ጎፋ ያልተለየ አፈርም መሬትም አለ፡፡
ኢትዮጵያን ሀገሬ የምንለው ከደቡብ እስከ ሰሜን፤ ከምእራብ እስከ ምስራቅ ጠዋት ማታ ሮጠን ተሯሩጠን ስለኖርበት አይደለም፡፡ የኢትዮጵያ ጥቂት መሬት ተቆንጥራ ለሱዳንም ሆነ ለሶማሊያ ልትሰጥብን ስትል በወኔና አትንኩኝ ባይነት እንቢ የምንለው ልጆቻችን ከአዲስ አበባ ተነስተው አኮቦ፣ ሞያሌ፣ ትሪፕሌክስ ወይም ባድመ ስለሚማሩ አይደለም፡፡ የኢትዮጵያ ጫፍ ራስ ካሳ ከሰሜን፤ ራስ ዱሜ ከምስራቅ፤ ሩዶልፍ ከደቡብ፤ ኑብያ ከምእራብ ነው ስንል እኮ መሬቱ ይታረሳል አይታርስም፤ መሬቱ ልማታዊ ነው አይደለም፤ ህዝቦቹ በቋንቋ ይመስሉናል፤ በአኗኗር ከእኛ ጋ አንድ ናቸው፤ ፎቅ ይገነባበታል አይገነባበትም፤ መሰረተ ልማት አለው የለውም ብለን አይደለም፡፡ እንደዛ አይደለም ሀገር ወገን ማለት፡፡ ሀገር ወገን ማለት ትስስር ነው፤ እንዲህ ተብሎ የማይነገር ግን ውስጥ ለውስጥ የሚያግባባ፤ ያልተናገርነው ግን የሚጮህ፤ አያት ቅድም አያቶቻችን አጥንታቸውን የከሰከሱበት፤ ደማቸውን ያፈሰሱበት ያ ነው ሀገር ማለት፡፡ ማንም ምንም በሉ ሳይለን ውስጣችን በህቡዕ ተነጋግሮ ባንድነት የምንቆጣበት፤ ባንድነት የምንደሰትበት፤ ቢከፋፍሉንም ተከፋፍለን የማንቀርበት፤ ሀገር ማለት ይህ ነው የጋራ ስሜት፤ በቀዩ ደማችን ውስጥ በጉልህ የተፃፈ ኢትዮጵያዊነት፡፡
ሰዎች ተወልደው ያደጉበትን ሰፈር በሰላም በመልካም አጋጣሚ ሲተዉ እንኳ የሆነ አንዳች ውስጥን ፈንቅሎ ልውጣ ልውጣ የሚል፤ ልብ የሚረብሽ፤ አልቅስ አልቅስ፤ ቅር ቅር፤ ባር ባር፤ ሆድ የሚያባባ፤ ውስጥን ፍስስ… የሚያደርግ ነገር አለ፡፡ ይህ ስሜት ያለው ፈቅዶና ወዶ ተወልዶ ያደጉበትን፤ ወልደው የከበዱበትን ሰፈር ቤት ቀይሮ፤ ተድሮ አልያም ለልማት በሚል ሰበብ ሲነሱ ሊሆን ይችላል፡፡
ይሄኛው ግን ይለያል፡፡ በዝሆኖቹ ፀብ ነው፤ በዝሆኖቹ እርስ በእርስ ግፊያ፤ ሳሩን በግል ለመቆጣጠር ካላቸው የበዛ ፍላጎት፤ ዱር ገደሉን ለዘመድ ላዝማዳቸው ለማስገበር ሲሉ፤ እንደልባቸው በሜዳው በሸንተረሩ ላይ ያለ ሀይ ባይ ለመቦረቅ ካለ ፅኑ ፍላጎት፤ ከርሀብ ሳይሆን ከበዛ ጥጋብ የተነሳ ፍልሚያ፤ ከትልቅ ሳይሆን ከትንሽ አእምሮ የተፈለፈለ የፍራቻ ስሜት፤ ከውስጥ ማነስ እላይን ለማግዘፍ በሚደረግ ጥረት ውስጥ ባለ ትግል የተፈጠረ መከራ ነው፡፡
በዚህ የትንሾች ትንሽ አስተሳሰብ ውስጥ ዊንታና ሀበንን አጣሁ፤ ልጅነትን በመለያየት ሰበብ ተቀማሁ፤ ሀገሬ ለዊንታና ሀበን ቦታ ስላጣችላቸው ነገም ለኔ የምትነፍገኝ መሰለኝ፤ እኔ ብቻ ሳልሆን እናቴም ውሃ አጣጪ ጎረቤቶቿን ማጣቷ እጅጉን አሳዘናት፤ ነገ ደግሞ እኛንስ እንደማያባሩን ምን ዋስትና አለን? ሰፈሬ ሰፈር አልመስል አለኝ፤ ምክንያቱም ዊንታና ሀበን የሉማ፤ ምክንያቱም የነ ዊንታና ሀበን እናት የሉም፤ ካፖርተኒው ኳስ፤ ድብብቆሽ ጨዋታው፤ አባሮሽ፤ ሌባና ፖሊሱ፤ ሱዚና ካሬው፤ ቃጤ ቃጤና አቦሰም ከማን ጋ ልጫወት፡፡ ተፈርዷል ስለዚህም እኩዮቼን ላጣቸው ግድ ሆነ፡፡
ኤርትራን ክፉ ዘመን ወስዶ ደግ ዘመን እንደሚያመጣት አምናለሁ፡፡ ዛሬም አዲስ አበባ ላይ ቁጭ ብሎ ዳኽላክን የሚያይ፣ የሚጠብቅ፣ የሚናፍቅ ልብ አለኝ፡፡ ብዙ አመት ቢያልፍም ዛሬም ዊንታና ሀበን ይናፍቁኛል፡፡ የልጅንት ወዳጆቼ ዛሬ አግብተው ቢወልዱም ልጆቻቸው ከልጆቼ ጋ እንዲጫወቱ እፈልጋለሁ፤ ከእነሱም ጋ የልጅንቴን እያነሳሳሁ መጫወት እፈልጋለሁ፡፡ ዳግም አንድ ሰፈር እንድንሆን አፈልጋለሁ፡፡ እነ ዊንታና ሀበን ኢትዮጵያዊነት ከምንም ከማንም በላይ እንደሚሰማቸው አውቃለሁ፡፡ እኔም ኤርትራ ወደ እናት ሀገሯ እስክትመለስ ድረስ ስለ ዳኽላክ ዝም አልልም፤ ስለ አሰብም ጸጥ አልልም፡፡
ኤርትራ መቼም አልረሳሽም!!!

0 comments