Sunday, October 4, 2015

የአይጦች ግልቢያ (Rat-Race



የዘር (የብሔር) ፖለቲካ አቀንቃኞች የአንድን ብሔር ማንነት ከሚኖርበት ቦታ (ጂኦግራፊ) ጋር ብቻ የሚያያዙበት አመለካከት አንድምታው ብልጠት የተሞላበት የፖለቲካ ጨዋታ ነው፡፡በጫወታውም የጫወታው ፈጣሪዎች ቀመራቸው ያለ ምንም እንከን ላስፈፃሚነት አስቀድመው በታጩት ዐይጦች ተግባራዊ እየሆነላቸውም ነው፡፡ 
የዚህ ፖለቲካዊ ጫወታ እሳቤም ሆነ የተጫዋቾቹ አይጦች ተግባር ሮበርት ቲ.ኪዮሳኪ የተባለው አሜሪካዊ ባለፀጋ በአለማችን ላይ ያሉ ባለፀጎችና ድሆች መካከል ያለውን ፤ ገንዘብ ባላቸውና በሌላቸው ሰዎች መካከል እየሰፋ የመጣውን ቅጥ የለሽ የሀብት ልዩነት መሰረት ላይ ያተኮረው “ ካሽ ፍሎው” የተሰኘ የሰሌዳ ላይ ጌም አሊያም “ራት ሬስ” ብሎ ከሚጠራው ጫወታ ጋር በብዙ መልኩ ይመሳሰልብኛል፡፡ 
ምክንያቱም ባንድም ሆነ በሌላ መልኩ ከኢህአዴግ ጋር ባንድነት የተሰለፉም ሆነ በአክራሪ የዘረኝነት አመለካከታቸው በተፃራሪ ሀይልነት የተሰለፉ ግለሰቦችም ሆነ ቡድኖች የዚህ የአይጦች ግልቢያ ውድድር ጫወታ አካል ናቸው፡፡ለዚህ ክፋት ወለድ ፖለቲካዊ እሳቤ ጠንሳሾች ሁለቱም አካላት የስውር ተልዕኳቸው ማስፈፀሚያ ወርቃማ አጋሰሶች ናቸው፡፡ለዚህ ቀመር ፈጣሪዎች የሁለቱም ወገን ጫፍ የያዘ የጋሪ ፈረሳዊ የአንድ መስመርተኝነት ጭፍን አመለካከታቸው ለኳስ አበደች ጫወታው ማድመቂያ ፤ ደጋፊውም ሆነ ተቃዋሚውም እኩል አስፈላጊና የሆኑበት ለተግባራዊነቱ ያላቸው ሚና ተመጣጣኝ በመሆኑ ነው፡፡በሁለቱ አይጦች መካከል ያለው ልዩነት የስርዓቱ ተጠቃሚ የመሆንና ያለመሆን ጉዳይ ብቻ ነው፡፡ 
ደጋፊና ተቃዋሚ አይጦች ለዓላማው ማስፈፀሚያ መሳሪያ ከመሆናቸውም በላይ፣አንዱን ብሔር ከሌላው ብሔር ጋር የጎሪጥ እንዲተያይ የጥላቻ ዘር በመዝራት እርስ በርስ በማናከስ ሁለቱም የቤንዚንነት ሚናቸውን በተገቢው መልኩ እየተወጡ በመሆኑ ለስርዓቱ መደላደያ ምቹ መደብ ሆነዋል፡፡ የዚህ ክፋት ወለድ ፖለቲካዊ እሳቤ ጠንሳሾች የስልጣን ዕድሜያቸውን ለማራዘም፤ በዚህ እንካሰላምቲያ መሀል የራሳቸውን ወገን ኢኮኖሚያዊ ተጠቃሚነትና የበላይነት ለማረጋገጥ በተለያዩ መስኮች በደህንነት መረብ፣በተለያዩ ትምህርት መስኮች ዕውቀታቸውን እያጎለበቱ፣በቴክኖሎጂ፣በመከላከያ ሐይል ግንባታ ወገናቸውን እያበቁ የማይነቀነቅ የአንድ ብሔር የበላይነት የነገሰበት ሰርዓት ለመገንባት እንዲያስችላቸው አይጦቹን በቀጥታም ሆነ በተዘዋዋሪ መንገድ እንደ ፈለጉት ይጋልቧቸዋል ያስጋልቧቸዋል፡፡ 
አይጦቹም በደመነፍስ ይጋልባሉ ሌላውን ንቃተ ህሊና የጎደለውን የማህበረሰብ ክፍል ማዘናጊያነት፣ ለግዜ መግዢያ ታክቲክነት በተቀመመላቸው መርዝ እራሳቸው ተመርዘው በዕውቀት ማነስ ዘአሊያም በጥቅም ተገዝቶ የሚከተላቸውን ተከታይ በመመረዝ ሀገራዊ የፖለቲካ መስመር ተፈላጊው አንድ ቅኝታዊ አመለካከት ሰለባ እየሆነ እንዲመጣ በሀገርቤት ባለውም ሆነ ዲያስፖራ ተብዬቀዎቹ ጋር የሚንፀባረቀው ሰሞንኛው የአይጦቹ ሁለት ጎራ የለየ የዘረኝነት መንፈስ ምስክር ነው ፡፡ 
ከአፄው ስርዓት ይዞ በዩኒቨርስቲ ተማሪዎች ፊት አውራሪነት ይቀነቀን የነበረው የብሔር እኩልነት ጥያቄ በተሳሳተ አመለካከት ላይ እንዲገነባ፣ባለፉት ስርዓት በርግጥም ግፍ የተዋለበትን የማህበረ ሰብ ክፍል ራስህን በራስህ የማስዳደር መብት ህገ መንግስቱ አውርሶሀል በሚል ሽንገላ ከራሳቸው ጥቅም ባሻገር ለወገናቸው ህልውና ግድ የሌላቸው ሆድ አደሮችን በማቀፍ በጅ አዙር ብዙሃንን ለመርገጥና ለመጨቇን እንዲያስችል ታስቦ በሸረኞች የተቀነባበረው የፖለቲካ ጫወታ ግዜ እየጠበቀ፤ መልክና ቅርፁን እየቀየረ የሚፈነዳ ቦንብ መሆኑን እያየን ነው፡፡ዛሬ ልንክደው ልንሸፍነው በማንችለው ስፋትና መጠን ከአንድነታችን ይልቅ ልዩነታችንን እንደ ዳዊት እንድንደግም እያደረገ ያለ
የክፉዎች ክፉ ዘር ነው ፡፡ 
ለዚህም ኢህአዴግ ወደ ስልጣን ከመጣበት ግዜ አንስቶ እስከ ዛሬ ድረስ የተቃዋሚ ፓርቲዎች የልዩነትና ህበረት ማጣት መንስዔ፤የአንድ ብሔርተኝነት ፖለቲካዊ አጀንዳ በመሆን የለውጥ እንቅፋት ከመሆኑም በላይ በአርሶ አደሩ፣በአርብቶ አደሩ መካከል በድንበርና መሬት በተለያዩ ግዜያት የተነሱ ግጭቶች አንስቶ እስከ ፊደላውያኑ ፅንፍ ዘመምተኛ የዘረኝነት ፖለቲካ አቀንቃኞች የቃላት ጦርነት ሳይገደብ እስከ ትጥቅ ትግል መድረሱ፣በተለያዩ ወቅቶች ዩነቨርሲቲ በዘለቁ ተማሪዎች ተቃውሞና አመፅ እየታጀበ፣በተለያዩ ጎሳዎች እርስ በርስ ጦርነት ውስጥ እንዲገቡ ያደረገና እዚህም እዚያም እልቂት ያስከተለ የግፈኞች ድምፅ የሌለው መሳሪያ ነበርም እንደሆነም ይቀጥላል ዘረኝነትና የዘር ፖለቲካ፡፡የሰሞኑ የአዲስ አበባን የማስፋፊያ ማስተር ፕላን ተከትሎ በማህበራዊ ድህረ ገፆች የምንመለከተው ምልልስና ሁለት ጎራ የለየ ስሜት መራሽ አተካሮ የዘረኝነትና ጠባብነት ልካችን የት ጋር እንደ ደረሰ የሚያሳይ አሊያም አውቀንም ሆነ ሳናውቅ የፖለቲካ ጫወታው ቀመር አስፈፃሚነት አይጣዊ ሚናችን ለመወጣት ደፋ ቀና እያልን ይሆንን?!... የሚያስብል ነው፡፡

0 comments