Thursday, November 12, 2015

*“እምረሐብ ይኄይስ ኮይናት (ከረሐብ ጦርነት ይሻላል)”* (፩)




*“እምረሐብ ይኄይስ ኮይናት (ከረሐብ ጦርነት ይሻላል)”* (፩)
(ሱራፌል ሐቢብ)
ሰው ለመብላት ባይኖርም ፤ ለመኖር ግን  መብላት ግዱ ነው፤ የማንኛውም ፍጡር ህልውና ከመብላት እና ካለመብላት ጋር የተቆራኘ ነው፤ የበላ ይኖራል፣ ያልበላ ደግሞ ይራባል ፤የተራበ ደግሞ ርሐቡን ማስታገሻ ካላገኘ መኖሩ ያከትማል፤ በግልፅ ቋንቋ ይሞታል፡፡ ረሐብ ጊዜ አይሰጥም ፣ ከመብልም ውጪ ማርከሻ የለውም፡፡  አንድ ግለሰብ የሚበላው አጥቶ ቢቸገርና በጠኔ ቢሞት፡- “ሰርቶ አይበላም ነበር”፣ “ሰነፍ” ፣ “ለአንድ ራሱ መሆን አቅቶት ነው” እና የመሳሰሉት ዓይነት የወቀሳ ትችቶች ከመቃብሩ በላይ ሊሰሙ ይችሉ ይሆናል፤ ነገር ግን አንዲህ አንደአሁኑ 15 ሚሊዮን ሕዝብ በረሐብ አለንጋ ሲገረፍ፤ ለሞትና፣ ለስደት ሲዳረግ ማን ነው ተወቃሹ? ማንስ ነው ለዚህ ችግር መስፋፋት ተጠያቂ? ማን ነው እርሱ ኃላፊነቱን ሊወስድ የሚገባው?
የረሐቡ ሰበብ  በአየር ንብረት ለውጥ ሳቢያ በተከሰተ የዝናብ እጥረት ይሁን በሌላ፤ አንዴት አስቀድሞ ከተነገረን ለችግሩ ተጋለጭ ከሆነው 2.5 ሚሊዮነ ሕዝብ መጠን አለት ተለት በማሻቀብ ዛሬ ላይ 15 ሚሊዮን ደረሰ? ችግሩስ ለምንና አንዴት በጊዜ ሂደት የሚያካልለውን የሀገሪቱን የቆዳ ስፋት መጠን እያሳደገ መጣ?
አንዲህ ሐገር በሚሊዮን የሚጠጉ ዜጎቿ በረሐብ ችግር ሲናጡ፣ ሲሞቱና ሲሰዳዱ፤ ተጠያቂው፣ ተወቃሹና ኃላፊነቱን ሊወስድ የሚገባው ሀገሬውን የሚያሰተዳድረው መንግስት አንጂ በረሐቡ ጅማሬ ወቅት ከብቶችን ውሀ ወዳለበት ስፍራ አላንቀሰቀሱም  ተብለው የተወቀሱ ምስኪን የረሐቡ ገፈት ቀማሾች የሆኑ አረኞች አይደሉም፤  ችግሩ የሚፈታው  “ራሳችንን በምግብ ችለናል፣ ችግሮቿን በራሷ አቅም የምትፈታ ኢትዮጵያ ተገንብታለች፣ ለርዳታ የሚንሯሯጥበት ጊዜ አልፏል፣ እንኳን እኛ አውስትራሊያ እና ካሊፎርኒያ በድርቅ እየተሰቃዩ ነው……………ወዘተ” በተሰኙ ተራ ዲሰኩሮችና ውሸቶች ሳይሆን የሚናገሩትን በመስራትና በፍጥነት ለችግሩ መፍትሔ በማፈላለግ ነው፡፡ እናንት ገዢዎች ሆይ፡-  ረሐብ ጊዜ አይሰጥም በመሆኑም በተራ ዲሰኩርና ሐሰት ጊዜን ከማባከንና አንዲህ አንደአሁኑ ችግሩን ከማባባስ ረጂዎችንና ሕዝቡን ያሳተፈ መፍተሔ ፍለጋ ላይ መሰማራቱ  ይበጃችኋል፡፡ በተራ ዲሰኩር የመፍተሔውን ጊዜ አያባከናችሁ ለረሐብ ችግርና አርሱን ተከትሎ ለሚከሰት የሞት አደጋ የሚጋለጠውን የወገኔን ቁጥር በየሳምንቱ በእጥፍ አታሳድጉት!! የዘመናት ውሸታችሁ ዓይኑን አፍጦ በመጣ ትልቅ አውነት ተጋልጧልና! ከእንግዲህስ ምን ማለት ይቻላችኋል??!!
“ከረሐብ ጦርነት ይሻላል” አንዲል ቅዱስ መፅሐፍ የረሐብን ኃያልነት እና ፋታ አይሰጤነት የሚያጤን ሕሊና ሊኖራችሁ አንደሚገባ ሊነገራችሁ አይገባም!!!
   

0 comments