Thursday, October 29, 2015

ጭን-ገረድነት፣ውሽምነትናቅምጥነት ባለትንሳዔው ትውፊታችን


#ክንዴነህ ታመነ #Kindeneh Tamene

እንዴት ከረማችሁማ ብዬ ጥሁፌን ልጀምራት አልኩና የኤፍሬም እንዳለ ወግ ልትሆንብኝ ሆነ…የቀኑ ደመናማነት ሀገሩን የጥጥ ማሳ አስመስሎታል….ሰማዩ በተራው ጭጋጋማ ቀለም የተቀባ የሰዓሊ ሸራ ይመስላል… ፀሐይት እንደ አብዮት ልጆቿን ቀርጥፋ ልትበላ አደባባይ የወጣች ነፍጠኛ ትመስላለች ብዬ ልጀምር አሰብኩና በዕውቀቱ ስዩም በሀገራችን ድርሰት ፅሁፎች መቼት ገለጻ ላይ  ያፌዘባት ጥሁፉ ትዝ ብትለኝ … ጥሁፌን እንዴት ብዬ ልጀምራት ይሆን ሀሳብ ተቸንክሬ ሰዐታት ነጎዱ…ኤዲያ ደግሞ እንዴት ልጀምር ብሎ በሃሳብ መንፏቀቅ ምን ይሉት ጅልነት ነው ብዬ ወዲያ ትቼው ልነሳ ሲዳዳኝ አንድ መላ ተዘየደችልኝ…እኔ እስከማውቀው ከሀገራችን ጠሀፍት ውስጥ ጥሁፉን በመፈክር የጀመረ ጠሀፊ ያለም አይመስለኝ …እቺ ያልተበላባት የጥሁፍ መጀመሪያ ስልት ናት…ፈክሮ መጀመር ልዩ ብልሀት ናት…እንግዲህ ግራ እጃችሁን እያነሳችሁ አብረን እንፈክራለን…ዳይ ወደ ፍከራችን !!
የነገደ ሰለሞን ስርወ መንግስታት ያወረሱን የነቃ ማህበረሰብ መለያ የሆነው የጭን-ገረድነት ባህላችንን ጠብቀን ለተተኪው ትውልድ እናስረክባለን!!
ፖለቲካዊ ውሽምነት ለህዳሴያችን መረጋገጥ ዋስትና ነው!!
ህዝባዊ ቅምጥነት የልማታችን ማሳለጫና ሀገራችንን ከፀረ-ልማት ኃይሎች ምንታደግበት የተባበረ ክንዳችን መገለጫ ነው!!
ጭን-ገረድነት፣ውሽምነትና ቅምጥነት ሰፊው ህዝባችን በሀገሩ ፖለቲካ  ውስጥ ያለውን ተሳትፎ የሚያረጋግጥበት የተሞክሮ መድረክ ይሆናል !!
አሁን ከፍከራ ብዛት የዛለ ክንዳችንን ለልማታዊ ሐሳባችን እናውለው፡፡ከዚህ ቀደም  “የአይጦች ግልቢያ” ወይም “ራት ሬስ” ብዬ የጣፍኳትን ጥሁፍ ያነበባችሁ ሰዎች ምን ይዘባርቃል እንዳትሉ በቀደመው ፅሁፌ ለማንሳት የወደድኩት ሃሳብ በሀገራችን ፖለቲካ ውስጥ በተቃውሞ አሊያም ፅንፍ በያዘ ዘርና ዘረኝነትን መሰረት ባደረገ የፖለቲካ አጀንዳቸው ጎራ የለዩ ወገኖችና እንዲሁም (የገዢው ፓርቲ ልሂቃን እንደሚሉት ፖለቲካ ሐይማኖት አይደለም፤ማንኛውም ጥቅሙ የተከበረለት አካል የፓርቲው የተባበረ የኃይል ክንድና የአውራ(ሬ) ፓርቲው ቀጣይ ህልውና መሰረት ይሆናል በሚል ፍልስፍናና ፖለቲካዊ ብልጠት ከጊዜና ከወቅት ጋር እየተሰናሰለ በሚቀረፅ ፖለቲካዊ ስትራቴጂ  ለአዳዲስ አባላት ምልመላ ፓርቲው ከሚሠጠው ትኩረት በላይ የተወሰነ የህብረተሰብ ክፍልን የጥቅም ተጋሪ በማድረግ ጊዜያዊ ጥቅሙ የተከበረለት በጥቅም የታወረ  ጭፍን ደጋፊ የማበራከት ፖለቲካዊ መሰሪነት ተጋላጭ(ቨልነራበል)የሆነው ክፍልና በጭፍን ደጋፊነት  ጎራ የተሰለፈው ወገንና  የተቃውሞ  ፖለቲካዊ የትግል ጎራ የተበጣጠሰና ከሚያቀራርበው ነገር ይልቅ የሚያራርቅ የብሄርተኝነት አጀንዳቸው  ለገዢው ፓርቲ ዕድሜ ማራዘሚያነት የተቀመመ የዘር ፖለቲካ መርዘኛ  እሳቤ የማስፈፀም አይጣዊ ሚናቸውን እየተወጡ መሆናቸውን ለማሣየት ያሰበ ነበር፡፡የዚህን ጥሁፍ ሙሉ ሃሳብ ማንበብ ከፈለጉ ወረድ ብለው ገፄን ይመልከቱ፡፡
ለዚህ ፅሁፌ መነሻ የሆነኝ ከአበዋዊ ብሂል፣ባህል ጋር የተሰናሰለ ዘመናዊነት እና ቇቅነት የወለደው ፋሽን አሊያም የመተጣጠፍ አኗኗር ዘይቤ፤ ያባትህ ቤት ሲዘረፍ አብረህ ዝረፍ ጭን-ገረዳዊ ፖለቲካዊ ማንነት፤እናቴን ያገባ ሁሉም አባቴ ነው ባይ ውሽማዊ ኢትዮጵያዊ ጠባይ፣ወይ ካለው ተወለድ ወይ ካለው ተጠጋ ሀገርኛ የቅምጥነት አመለካከት ሰዋዊ ስብዕናን ሽባ አድርጎ የሚያስቀር የአመለካከት ልምሻነት ከትውፊት፣ከባህል፣ከሐይማኖት እና ፖለቲካዊ ስርአቶች ጋር ያላቸውን ቁርኝትና የዛሬው ጉራማይሌ ሀገራዊ አመለካከታችን ሰበበ መንስዔ  ይሆናል ያልኩትን ግላዊ ምልከታዬን ማቋደስ ነው፡፡በኔ እምነት ፅንፍ የያዙ ድጋፍና ተቃውሞ ፖለቲካዊ አመለካከቶች ከነጉድፋቸው በምንም መስፈርት ከላይ ካነሳሁት የአመለካከት ልምሻነት ጋር  ለንፅፅር እሚቀርቡ አይደሉም፡፡የሰው ልጅ ለሚያምንበት ነገር፣ለሚያምንበት ዕውነት መቆሙ የሰውነቱ መገለጫ ነው፡፡ዕውነቱና ዕምነቱ እንዲሁም የቆመለት ዓላማ ሀገርና ወገንን ታሳቢ ያደረገ ነው?...የሰፊውን ህዝብ የባህል፣የሐይማኖት፣የብሔር ነፃነት አስጠብቆ ሀገርን በጋራና ባንድነት ሚያራምድ  ነው ዓላማው?በሚለው ጉዳይ ላይ ያለን ልዩነት እንደተጠበቀ ሆኖ
በግሌ የትኛውም ግለሰብ ሆነ ቡድን ቆሜለታለሁ የሚለው ፖለቲካዊ አላማ ቅዱስ አሊያም እርኩስ ነው ብለን እምናወድስበትና እምንኮንንበት ሁላችንንም ሊያስማማ የሚችል መስፈሪያ ባይኖረም…ግለሰቡ ወይም ቡድኑ የያዘው መስመር ሰይጣናዊ ይሁን መላዕካዊ፣ቅዱስም ይሁን እርኩስ ፣አጥፊም ሆነ አልሚ ቢያንስ የቆመለት፣የሚቆምለት ዓላማ አለው፤ቢያንስ የሚገድልበትና የሚሞትለት ምክንያት አለው፡፡በተመሳሳይ ከጭፍን ጥላቻና ከጭፍን ደጋፊነት የራቀ በአመክንዮ ነገሮችን የሚመረምር አድማጭ ያጣ በሀገሬ ጉዳይ ላይ ያገባኛል የሚል ሐቀኛ ሀገር ወዳድ የሆነ ኢትዮጵያዊ  ውስን ቢሆንም መኖሩ የማይካድ ነው፡፡ዛሬ ላይ ግን ኢትዮጵያና ኢትዮጵያዊነት የጭን-ገረድ፣የውሽማና የቅምጥ  ፖለቲካዊ ስብዕናና ማንነት ያዳበሩ ሰዎች ምድር ሆናለች፡፡
በዚህ ጥሁፍ ቀጣይ ክፍል  ከላይ በርዕሱ የተመለከትነው በቀደመው ስርዓት ነገስታትና ባላባቶች  በሀይማኖታዊ መሰረት ላይ የገነቡት  ማህበረሰባዊና ፖለቲካዊ ስብዕናና ኢትዮጵያዊነት ከነገስታቱ ወሲባዊ ጠባይ ጋር እንዲመቻመች ያደረጉት የጭን-ገረድነት፣ውሽምነትና ቅምጥነት ዐመል በግዜ ሂደት ባህላዊ መሰረት መያዙና በተራው ማህበረሰብ ሳይቀር እንደ ትከክል ተወስዶ ተቀባይነት አግኝቶ ማህበረሰባዊ ወሲባዊ ጠባይ ለመሆን የበቃው በአዝማሪ ዜማና ግጥም ሳይቀር ባል በሚስቱ ላይ፣ሚስት በባሏ ላይ መወሸም፤በሚስት ላይ ቅምጥ ማኖር የወንድነት መገለጫ ተደርጎ ለውዳሴ የሚያበቃ መልከጥፉን በስም ይደግፉ አይነት ማህበረሰባዊ ነውር“እዚህ ጋር እኔ ነውር የሚለውን ቃል ለመግለፅ የተጠቀምኩት ድርጊቱን በመሰረታዊነት የክርስትና እምነት ተከታዩ  ማህበረሰብ ከምንም በላይ በሚያምናቸው የክርስትና መምህሮቹ ሐይማኖታዊ አስተምሮዎች  ጋር ድርጊቱ የሚጣረስና ባንድ በኩል እራሱም ነውር  ብሎ ስለሚኮንነው ነው፡፡
በሌላ በኩል የጋብቻን ቅዱስነት፣አንድ ወንድ ለአንድ ሴት መፅሐፍ ቅዱሳዊ አስተምሮ፤ በአይኑ አይቶ በልቡ የተመኘ አመነዘረ የሚለውን ከአስርቱ ትዕዛዛት አንዱ የሆነውን ሀይማኖታዊ ቀኖናና  የዕምነት ድንጋጌ ጋር በፍፁም የሚቃረነው “ከዝሙት የሚቆጠረውን ኩነኔያዊ ተግባር”በባህልና  በፖለቲካዊ ትክክለኝነት ሂሳብ  ሁለት ፍፁም ሊጣጣሙና በአንድ ሐይማኖታዊ አስተምሮ የተቃኘ ስብዕና ውስጥ ተቻችለው ሊገኙ የማይችሉ፤ሁለት ፅንፍ የያዙ አመለካከቶችን አንድ ማንነት ሊቀበላቸውና ሊተገብራቸው የሚከብዱ መንታ ጠባያት እርስ በርሳቸው በሚጣሉ ማቶ ተረቶች እያስታከከ ከትውልድ ትውልድ እየተላለፈ የመጣ አበዋዊ ባህልና ሐይማኖትን የቀየጠ በሁለት ቢላ የመብላት፤ባንድ ራስ ሁለት ምላስ አመለካከት ለዛሬው የተምታታ ኢትዮጵያዊ ስብዕና፣ማንነት መሰረት ነው ባይ ነኝ፡፡እርግጠኛ ባልሆንም ስለዚህ ሀገራዊ ፖለቲካዊ ስብዕና ሌሊሳ ግርማ የሚባል ጠሀፊ አዲስ አድማስ ጋዜጣ ላይ የጣፈውን መጣጥፍ ያነበብኩ ይመስለኛል፡፡
ትክክልና ስህተት ብሎ እራሱ የፈረጃቸውን ሁለት አብሮ አይሄዴ አመለካከቶችን በእኩል ተቀብሎ የሚኖር ሁለቱንም እያጣቀሰ ልቡን ለእግዘኤር ጭኑን ለሰይጣን ሚገብር፣ሰይጣንን ባደደባባይ የሚኮንንና የሚያብጠለጥል በጓዳው ሰይጣንን የሚያከብር ማህበረሰብ፣ሲያሻው ባደደባባይ ሙስናና ሙሰኞችን የሚጠየፍ፣ሌባ እጅ ከፍንጅ ያዝኩ ብሎ ተባብሮ እንደ እባብ ጭንቅል ጭንቅሉን  የሚቀጠቅጥ በሌላ በኩል እከሌ ከመንግስት ካዝና ይኼን ያህል ሚሊየን ብር ሰረቀ ሲባል እንዲህ ነው እንጂ እናቱ የወለደችው እያለ የሚያሞካሽ፤ለአፉ ሌብነትን የሚጠየፍ  በልቡና በተግባሩ ግን ሌቦችን የሚያደንቅ፣ሲሾም ያልበላ ሲሻር ይቆጨዋል እያለ ሚተርትና ስትሾም ካልበላህ ከንቱ ነህ እያለ ሚያጀግን፤ እርስ በርሱ የሚጣረስ  አንዱ ሌላውን ደግፎ ሊቆም በማይችል አመክንዬ በጎውን ከክፉው ያዳቀለ ድቅል ኢትዮጵያዊ ማንነት፣ክልስ ኢትዮጵያዊ ማንነት ውዥንብራችንን መለስ ብለን ብንቃኘው ምን ይለናል፡፡ከዚህ በመለስ አለማየሁ ገላጋይ በወሬሳ ልቦለዱ ተረታችንና የተምታታ ስብዕናችን ዋዘኝነት ጋር አዋህዶ ሊያሳየን የፈለገው ይሄንኑ መለቲፕል ፐርሰናሊቲ የተጠናወተው ጠባያችን ይመስለኛል፡፡
ይህቺን ሊንክ ከልከው https://www.facebook.com/kindeta ዘለቅ ብለው ያንብቡኝ!!... እርሶም የመውደጃ ምልክተዋን ተጭነው መውደድ- መዋደድዎን አይርሱ?! ለወዳጅዎም ግብዣ ይላኩ፡፡

0 comments