Monday, September 14, 2015

ያ ትውልድ Vs ይህ ትውልድ

ያ ትውልድ Vs ይህ ትውልድ
(ቃልኪዳን ኃይሉ)
 (ከለምን አትቆጣምና ሌሎችም መጽሐፍ የተወሰደ)
እኔ ብቻ ሳልሆን ብዙዎች የሚያውቁት የሚያደንቁት ደራሲ አለ፡፡ አንድ መጽሐፍ ፅፌ ጨርሼ እንዲገመግምልኝ አይቶም ከወደደው መግቢያ ወይም የጀርባ ጽሑፍ (blurb) ቢጽፍልኝ ብዬ ነው ወደዚህ ታዋቂ ሰው የሔድኩት፡፡
ከተዋወቅን በኋላ ብዙ አውርተናል፡፡ ቀጥሎም ጽሑፌን ሰጥቼው ነበር እና እየደወልኩ ስጠይቀው “ማን ልበል?” ይለኛል፡፡ ቢያንስ በሳምንት አራት እና አምስቴ እደውልለታለሁ እሱ ግን ሁልጊዜ “ማን ልበል? ማን ልበል?” ይለኛል፡፡ ገባኝ ስልኬን መያዝ አልፈለገም እሺ መብቱ ነው አንድ አንጋፋና ዝነኛ ደራሲ የዚህን “የግልብ” ትውልድ ስልክ መያዝ አይመጥነው ይሆናል፡፡ ግን ተደጋጋሚ የሚደውልለትን ድምጽ መለየት እንዴት ያቅተዋል? ይሁን አልኩ፡፡ በአካል ስንገኛኝ ግን “ለምን ስልኬን ‘ሴቭ’ አታደርገውም? ለምን ሁሌ ማን ልበል ትላለህ?” ስል ጠየኩት፡፡
አንጋፋው ደራሲ እንዲህ ሲል መለሰለኝ፡፡ “እናንተ ምናችሁ ‘ሴቭ’ ይደረጋል፡፡ እናንተ ምንስ ሀሞት አላችሁ? ምንስ አይነት ልብ አላችሁ? የሰውነት ክብሩስ ይገባችኋል? ሀገር፣ ትውልድ፣ ማንነት፣ ለመሆኑ ይህች ሀገር የእናንተ ትመስላችኋለች? ታላቅነትን… ታውቁታላችሁ? አታውቁትም፡፡ ስለዚህ እናንተን እውቅና ሰጥቶ ሴቭ ማድረግ ይከብደኛል፡፡” በማለት ድስኩሩን ቀጠለ፡፡
“እኛ እኛ እኮ እንዲህ አልነበርንም፡፡ እናንተ ለብ ለቦች ናችሁ፡፡ ብትሄዱ አሜሪካ፤ ብትለብሱ እንደ አሜሪካውያን፤ ብትናገሩ እንደ ራፐር፤ ብታወሩ ስለሆሊውድ ፊልም፤ ቢናፍቃችሁ በርገርና ፒዛ፤ ብትማሩ የኢፌድሪ ሕገ መንገስት፤ ብታነቡ ስለ ወሲብ፤ ተምራችሁ ብታልፉ በኩረጃ፤ ተምራችሁ በትጨርሱ ስራ የላችሁ፤ ብታልሙ አሜሪካ፡፡ እኛኮ አሜሪካ ተምረን ኢትዮጵያ የሞትን፤ ፒኤችዲ ይዘን አሲምባ የተገኘን፤ አፄውን ጥለን ደርግን ያንቀጠቀጥን፤ ትምህርት እምቢ ብለን ጫካ የገባን፤ የማትሪክ ውጤት ይዘን ከትግል በኋላ ያልን፤ ሰው አይደለም ተራራ ያንቀጠቀጥን ነን፡፡ ታዲያ ከእናንተ ጋ እንዴት ነው የምንግባባው፡፡ እናንተ ይህ ሁሉ ይገባችኋል? አይገባችሁም፡፡ እናንተን እንዴት ነው ሴቭ የምናደርጋችሁ? ለብ ለብ!” አለኝ የግንባሩ ስሮች ተገታትረው፡፡
ለብ ለብ አንጋፋው ትውልድ ለአዲሱ የሰጠው ስም ነው፡፡ ያኛው ትውልድ የአሁኑን ወጣት ለብለብ፣ ግልብ፣ ሀሞተ ቢስ፣ ጥልቀትን የማያውቅ፤ እንደ ፊኛ በአየር ብቻ የተነፋ በትንሽ ነገር የሚተነፍስ ነው ብሎ ይፈርጀዋል፡፡
በመጀመሪያ ያ ትውልድ ማነው? ያ ትውልድ ጉልቤ፣ አስተዋይና አንባቢ ነው፡፡ አፄውን አውርዷል፤ ደርግን ታግሏል ብሎም ደርግን ጥሎ ለስልጣን በቅቷል፤ በደርግ ጊዜም ቢሆን አሌ የማይባል ስልጣንና ጉልበት ነበረው፡፡ ያ ትውልድ አሁንም ሙሉው ስልጣን በእጁ ነው፡፡
ይህ ትውልድ የእኔ እኩያ ነው፡፡ በኔ ግምት በተለይ ከ1970 ዓ.ም. በኋላ የተወለደ እሱ ወጣት ነው፡፡ ባዶ እጁን ያለ ወጣት በዛ ላይ ግልብ ምንም አያውቁም የምንባል፡፡ ግን አንጋፋው ትውልድ ለምንድን ነው? ግልብ ለብለብ የሚለን፡፡ ለብለብን ማን ፈጠረው? ግልቡን ማን ገለበው? አስኪ አንጋፋዎቹ ተጠየቁ? ቃሚ፣ አጫሽ፣ ጠጪ፣ ስደተኛ፣ ተስፋ ቢስ፣ ዘረኛ፣ አክራሪ፣ እውቀት አጠር ማነው ያደረገው?
ደራሲው “እናንተ” ሲል ይህን የኔን ትውልድ ለማመልከት ነው፡፡ የፈረደበት ትውልድ! ይህ ትውልድ ስም የለውም ምን ቢያደርግ ዝና ይርቀዋል፤ ምን ቢናገር እንደ ስልሳዎቹ ይባላል እንጂ እንደ ራሱ የሚል ስም የለውም፤ ስልሳዎቹ እንደፈለጉ ይጋልቡታል፤ ከሀብት እስከ የፖለቲካ ስልጣን ተቆናጠው መልሰው ይሰድቡታል ደሞ ይህ ትውልድ እያሉ ያበሻቅጡታል፡፡
“Child is the father of man” ይላል ታላቁ የስነ-ልቦና ሊቅ ሲግመንድ ፍሮይድ፡፡ ልጁ የሰውየው አባት ነው ለማለት፡፡ የዛሬ ልጆች ነገ አባት ናቸው፡፡ የትናንት ጥልቆች ዛሬም ጥልቅና አስተዋይ ልጆቹ ሊኖሯቸው ይገባ ነበር፡፡ ብርቱዎች (iron man)፣ አልበገር ባዮች፣ ባለ ስሁል መስተሐልዮች (mind)፣ ተራሮችን ያንቀጠቀጡ አባቶች፣ ባለ ራእይ፣ ቆራጥ፣ ለአላማ ታጋዮች… ያሳደጓቸው ልጆች ያው እንደነርሱ መሆን ነበረባቸው፡፡
ያ ትውልድ ምሁር ነው ያውም ካንጋፋ ዩንቨርስቲ እስከ አውሮፓና አሜሪካ የተማረ፡፡ አሁንም ትላልቆቹንም ሆነ አዳዲሶቹ ዩንቨርስቲ ድረስ ፕሬዝዳንት፣ ሌክቸረር፤ የዲፓርትመንት ዲን፤ የፋኩሊቲ ሃላፊ፤ የትምህርት ክፍል ሃላፊ፤ የትምህርት ሚኒስቴር… ነው፡፡ በሀገሪቱም ላይ ፈላጭ ቆራጭ ህግ አውጪ፣ እቅድ አስፈጻሚ፣ ጠቅላይ ሚኒስቴር፣ ፕሬዝዳንት፣ ትውልድ አራቂ ምሁር… ውጤቱ ግን ግልባጭ ነው፡፡ “የእሳት ልጅ አመድ” ያውም ብን ያለ ንፋስ ያግለበለበው አየር ላይ የቀረ ብናኝ፡፡
ተጠያቂው ማነው? ወጣቱ የኔ ትውልድ ነው ካላችሁ እኛማ በፍፁም አንጠየቅም እላችኋለሁ፡፡ በፍፁም! የኔ ትውልድማ ለሚመጣው ትውልድ እጣ ፈንታ ይጠየቅ እንጂ ለእሱነቱ ተጠያቂዎቹ አሳዳጊዎቹ ናቸው፡፡ መጽሀፉን ደብቀው “አሳይመንት” እንዲሰራ እያስገደዱት፤ “እረኛ” “ከብት” እያሉ ሞራሉን ያላሸቁት፤ ያነበበውን ብቻ እንዲያቀረሽላቸው ሸምዳጅ ትውልድ የፈጠሩ፤ ለልማት ሲባል ብቻ የነፍሱ ጥሪ ያልሆነ ትምህርት የጋቱት፤ ትምህርት ከአስር ጠላትን ከስር ብለው የተነሱት፤ እስከ አራተኛ ክፍል መውደቅ የለም የሚባል ፖሊሲ የቀረፁት፤ የድረስ ድረስ ትምህርት የሰጡን፤ የድረስ ድረስ ምርቃት የመረቁን እነማን ናቸው? ይህ ሁሉ ነገር የእናንተ የአንጋፋዎቹ ውጤት መስሎኝ? (በነገራችን ላይ በፖሊሲው ላይ አድራጊ ፈጣሪ ባንሆን እንኳን ጥፋትን አይቶ እንዳላየ ማለፍ ከተጠያቂነት አያድንም እንላለን እኛ ወጣቶች፡፡)
ትያትር ቤቱ፣ ፊልሙ፣ ማስታወቂያው፣ ቴሌቪዥን ጣቢያው፣ ሬድዮ ጣቢያው፣ ሆስፒታሉ፣ ህንፃው፣ የህንጻ ተቋራጩ፣ “ሞሉ”፣ ሀብቱ፣ ሚኒስቴር መስሪያ ቤቱ በእናንተ እጅ እኮ ነው፡፡ ይህን ሁሉ ይዛችሁ እኮ ነው የምትወቅሱን፡፡ ምንም ሳትሰጡን እኮ የምትተቹን፡፡ የተማርነው የእናንተን የትምህርት ፖሊሲ ነው፡፡ ያደግነው እናንተ የምታስተላልፉትን ፕሮግራም፣ ማስታቂያ፣ ዜና፣ ትምህርት፣ መዝናኛ… እየሰማን ነው፡፡ የገባ ነው የወጣው፡፡ ምርጥ ምርጡን ለህፃናት ሲባል እናንተ በተቃራኒው ለራሳችሁ አደረጋችሁት፡፡
ግን ለምንድነው ልምዱን፣ እውቀቱን፣ ታታሪነቱን፣ ሀገር ወዳድነቱን፣ ሀብቱን፣ ስልጣኑንም ጭምር የማትሰጡን? መልሳችሁ መቼም አትሰሙም፣ አይገባችሁም፣ ትበታተናለችሁ፤ ራሳችሁንም ማስተዳደር አትችሉም፣ ፅንፈኞች፣ ሱሰኞች፤ ለብ ለቦች ናችሁ ነው የምትሉን፡፡
“In the century of blind one eyed man is a king” ይህ መፈክራችሁ ነው፡፡ “በአይነስውራን ዘመን አንድ ዓይን ያለው ሰው ንጉስ ነው” እንደማለት፡፡ የማይረባ፣ የማይጠቅም፣ ሱስ ያናወዘው፣ ገንዘብ ያጠረው፤ አናሳ እውቀት ያለው ትውልድ የፈጠራችሁት እናንተ አንጋፋዎቹ (ያ ትውልድ) ናችሁ፡፡ ምክንያቱ ግልጽ ነው መረሳትን አትፈልጉም፤ ያ ትውልድ መባል ስለምትወዱ፤ በላምባ መፈለግን ስለምትሹ፤ አይ እነሱ! የመባል ጥማት ስላለባችሁ፤ በእኛ አላዋቂነት የእናንተን ታላቅነት ለማግነን፤ ቀጣዩን ትውልድ ስለፈራችሁት ነው፡፡
ሌሎች ፀሀዮች ቢኖሩ ኖሮ የአሁኗ ብቸኛ ፀሀይ እንዲህ ተናፋቂ እና ተወዳጅ አትሆንም ነበር፡፡ የጨረቃም ብልጠቷ በፀሀይ ፊት አለመውጣቷ ነው፡፡ የእናንተም ብልጠት ከእነዚህ ከዋክብት የተወረሰ ነው፡፡ በእኛ መሀል እናንተ ታላቅ ናችሁ፤ ለእኛ እናንተ አዋቂም ታዋቂም ናችሁ፡፡ ባለስልጣን፣ ባለሀብት፣ ምሁር፣ የዚህ እና የዛ ባለቤቶች ናችሁ መባል ያስደስታችኋል ትፍስህት ይሰጣችኋል፡፡
አንድ ላይ አድጋችሁ የተከፋፈላችሁ፤ እስከ አስራ ሁለተኛ ክፍል ተምራችሁ እኛን አስረኛ ላይ እንድናቋርጥ አደረጋችሁ፤ በጥለቀት ተምራችሁ በለብለብ አስተማራችሁን፤ ጥሩ ኑሮ ኖራችሁ በኛ ላይ አከበዳችሁት፤ በቂ መሬት ከያዛችሁ በኋላ የሊዝ ህግ አወጣችሁብን፤ የፈለጋችሁን እየተናገራችሁ ኖራችሁ ያውም ነፍጥ እሰከ ማንሳት፤ ምንሽር እስከ መተኮስ፤ ለእኛ ሲሆን ፀረ ሽብር ህጉን አፀደቃችሁብን፤ ንብረት በደንብ ከያዛችሁ በኋላ ንብረት እናስመዝግብ አላችሁ፤ ማስተርስ እና ዶክትሬት ዲግሪአችሁን ከያዛችሁ በኋላ መማርን እንደ ቅንጦት አያችሁት፤ ክፍያውን አስወደዳችሁብን፤ ጷጉሜን አንድ ላይ ተጠምቃችሁ ረመዳን ላይ አብራችሁ በብስኩት አፍጥራችሁ ዛሬ ሙስሊም እና ክርስቲያን አባባላችሁን… ማን? እንዳትሉኝ እናንተ ያ ትውልድ! ያ ትውልድ!
ባንወቃቀስስ?
ይህ ትውልድ የራሱ ስሜት አለው፤ በራሱ መንፈስ ሊመራ ይገባዋል፡፡ መለኪያው የስልሳዎቹ መንገድና ልክ መሆን የለበትም፡፡ ትውልድ ዘመኑን ነው የሚመስለው እንጂ አባቶችን አይተካም ግዴታውም አይደለም፡፡ ኃይል፣ ወኔ፣ ብልሀት፣ ጥልቀት አለው፤ ብዙ ያውቃል፤ አቅም አለው የሚባለው ትውልድ እኮ ታገልኩ ካለ ዛሬ ሊወቅሰን ሳይሆን ፍሬ ያለው ነገር ሊያቆይልን ይገባ ነበር፡፡
ኃይለኛ ነኝ ካለ ኃይሉ በንግግር ሳይሆን ለዚህች ሀገር ጠብ የሚል ነገር ሲያተርፍላት ነበር፡፡ ሞትኩላት፣ ደማሁላት፣ ከሰርኩላት፣ ሳልማር ታገልኩላት፣ ሳልጠገብ ጠመንጃ ተሸከምኩላት ብሎ ቀጣዩ ትውልድ ላይ ባልበላ አንጀቱ ዳግም ጠመንጃ ካሸከመ፤ ፋኖ ብሎ የወጣበት አደባባይ በእሱ ተራ ላይ አደባባዩን ካጠረ፤ አደባባዩን የባቡር መንገድ ካደረገ ትግሉ እምን ላይ ነው? ትግሉ ተረኛ ጨቋኝ ለመሆን ነው? ከድንጋይ በላይ ጥይትና ቦንብ የወረወረ ትውልድ ዛሬ ወረቀትና ብእር እንኳ እንዳይገናኙ ከከለከለ፤ ትናንትን የታገለው ለልጁ ጠመንጃን ሊያወርስ ነው ማለት ነው?
የዚህ ትውልድ ሀሞትና ወኔ የሚለካው ጠመንጃ ከያዛ ጋ ብሎም ካለፈው ልምዱ ብዙ የአገዳደል መንገድ የተማረን ትውልድ ላይ ጠመንጃ ስላላነሳን ነው? ዛሬ ሀሞተ ቢስ የሚለን፤ ከፈለጋችሁ ግቡና ሞክሩን የሚለን ምን ለማለት ነው?
“የእኛ ሩጫ ማራቶን ሳይሆን ዱላ ቅብብል ነው” ብለው ነበር የቀድሞው ጠቅላይ ሚኒስተር መለስ ዜናዊ፡፡ እኛ ደግሞ እንዲህ እንላለን ዱላ ቅብብሉን ከወሬ ይልቅ በተግባር አሳዩን፡፡ በእውቀት ላይ እውቀትን ጨምሩልን እንጂ ከእናንተ የተረፈው ብቻ አይድረሰን፤ ያላችሁን ልምድ እንዳለ ስጡን እንጂ እንደ ባንዲራ ተሰቅላችሁ እኛን ብቻ ቅዱስ ቅዱስ በሉን አትበሉን፤ እንመራረቅ እንጂ አንረጋገም፤ እንወዳደስ እንጂ አንቦዳደስ፤ በክብር ባንዲራውን እንረካከብ እንጂ አንነጣጠቅ፤ አሳድጉን እንጂ አደግድጉ አትበሉን፡፡
ኮፐርኒከስ ለሰር አይዛክ ኒውተን ሰጠ፤ ኒውተን ለአልበርተ አቀበለ ከአልበርት ደግሞ ለስቴፈን ሐውኪንግ እና ብዙ የፊዚክስ ጠበብቶች እውቀቱን ተቀብለው ለወደፊት እያሻሻሉት ነው፡፡ ይህ አውሮፓ እና አሜሪካ ውስጥ የሆነ የፊዚክስ እውቀት ሽግግር፤ የጠቢባን ቅብብሎሽ ነው፡፡ አባት በፍቅር ሲያስረክብ ልጅ በእውቀት እና በብርታት ይቀበላል፡፡ ለበለጠ መሻሻል እና መብቃት በሙሉ ኃይሉ ይሰራል፡፡ ምክንያቱም መተሳሰሪያው ፍቅር እና እውቀት ስለሆነ አባት ሳይጠየቅ ሳይለመን ለልጁ ስላስረከበ ልጅም ለመቀበል ዝግጁ እና ብቁ ሆኖ ስለተገኘ፡፡
መቀባበል እንዲህ ነው እንጂ ከቦታ ቦታ መቀያየር አይመስለኝም “ጉልቻ ቢቀያየር ወጥ አያጣፍጥም” አይደል የሚባለው፡፡ ቅብብሎሹ ቀናነት እና ፍቅር ከተሞላበት ለነገ ደስታ እንጂ ስጋት አይመስለኝም ችግሩ በግድ ስጡን ያልን እለት ነው፡፡ እናንተም እንቢ እኛም አምጡ የዛኔ…
ጨረስኩ ግን ከመጨረሰ በፊት እንዲህ ብል መልካም ነው፡፡ አላማዬ የኔን ትውልድ ቅዱስ አድርጌ ያን ትውልድ በጅምላ ልፈርጅ አይደለም፡፡ የጠፋ፣ የጎደለና ያልተሳካውን የቀድሞው ትውልድ ላይ ልደፈድፍ አልተነሳሁም፡፡ እኩዮቼን ከፍፁም ተጠያቂነት ነፃ ላወጣቸው አይደለም፡፡ ከላይ ያልኩት ሁሉ ያ ትውልድን ባጠቃላይ ፈርጄ አብሮ አደጎቼን ከችግሩ ነፃ ላወጣ በመሻት እንዳይመስላችሁ፡፡ የማወራው ብዙ ትችት በዚህ ትውልድ ላይ ስለበዛ እኛም እንዴት እንደምናያው እንድትረዱልኝ ነው እንጂ ለትውልዱ የወደቁ፣ የሞቱ፣ የተጋደሉ አሁንም የሚለፉና የሚታገሉትን እኛም ታሪክም አንረሳቸውም፡፡

0 comments