Saturday, September 26, 2015

“ተይ ሀገራችን”



“ተይ ሀገራችን”
             በዘመናችን ሐሰት ከአጥንትና  ደም ተሰርቶ  ፣በሰው አምሳል  ስጋ  ለብሶ  በተሸከርካሪ  ወንበር  ተቀምጦ አየተንፈላሰሰሰ  ከፊቱ ደምፅ ማጉያዎችን ፣ በቀኝና በግራው ቅጥፈቱን የሚነዙለትና የሚያራግቡለት ጋዜጠኛ ተብዬዎች ደርድሮ ውሸቱን ሲለቀው ያልተመለከተ ኢትዮጵያዊ ለመኖሩ እጠራጠራለው፤ በግምት ከወርና አስራ አምስት ቀን በፊት ይመስለኛል በሐገራችን ሰሜን ምስራቅ ፣ በስምጥ  ሸለቆና  የምስራቁ  ክፍል  ስለተከሰተው  ድርቅ  ይህ  ስጋ  ለባሽ  ሐሰት  የድርቁ  ሁናቴ የማያሰጋ ፣ መንግስትም ይህን አደጋ መቆጣጠርና መመከት አንደሚችል በድፍረት ተናገረ አንደውም እንኳን ሰው ሊሞት ቀርቶ አንስሶቹም የሞቱት በእረኞች ቅሽምና አንጂ በድርቁ ሳቢያ አንዳልሆነ አክሎ  ደሰኮረ መች ይሔ ብቻ የማንንም አርዳታና ድጋፍ አንደማይሻ አበክሮ ከገለፀ በኃላም በራስ አቅም ችግርን የመቋቋም እና የመፍታት ደረጃ ላይ የደረሰች ሐገር ዛሬ ላይ መፈጠሯን፣እራሷን በሙሉ አቅም መመገብ የቻለች ኢትዮጵያ መገንባቷንም አስረግጦ ሳያፍር እና ሳይፈራ በማን አለብኝነት ደሰኮረ፡፡

ይህ በሰው አምሳል የተገለጠ  ሐሰት ይህን ብሎ ባለ የሳምንት ጊዜ ውስጥ አለቃው በአንድ ትልቅ አዳራሽ ውስጥ “ራሳችንን በምግብ ችለናል፣ አንኳን እኛ ካሊፎርኒያና አውስትራሊያም በድርቅ እየተሰቃዩ ነው፣ ከዚህ በፊት ድርቅ ሲከሰት ሮጠን ወደ ውጪ ድጋፍና አርዳታ ልመና  ነበር የምንሔደው አሁን ግን ያ! ታሪክ ሆኗል………………….ምናምን  ምናምን” አሉና ተጨበጨበላቸው!!! ግና ያጨበጨቡ እጆች ግለት ሳይበርድ፣ የዲስኩሩና የጩኸቱ ድምፅ ርግብግቢት ሳይጎድል በዚህ በተገባደደው ሳምንት ይህ ሐሰተኛ አምሳለ ሰብእ በወትሮው ወንበሩ ላይ ፊጥ አለና ከፊቱ ለተደረደሩ ጋዜጠኞች ልማዱን ሊያደርስ ተደነቀረ፤ ከወር በፊት ስለተናገረው ረስቶ ይሆን (ውሸት'ኮ  ይረሳል) ወይም በተለመደ ማን አለብኝነት ተደፋፍሮ ይሁን ብቻ አኔ አልገባኝም! ፡ ስለድርቁ ሁኔታ ሲናገር የተጎጂዎች ቁጥር በእጥፍ አንደጨመረና፣ የተጎዱ ዜጎችን ለማቋቋም ከዓለም አቀፉ ማህበረሰብ የተጠበቀው ድጋፍ  አንዳልተገኘ መሰከረ፣ የውጪ ድጋፍና አርዳታ አንደሚያስፈልግ በመንግሰትና በረጂዎች ታምኖበት ወደ እንቅስቃሴ አንደተገባም ቃሉን ሰጠ፡፡

ታዲያ አስቀድሞ ጉራን መንዛት ለምን አስፈለገ? አውነቱን ለሚያውቀው የኢትዮጵያ ህዘብ ይህ ንቀት ነው!!! “ሆድ ሲያውቅ ዶሮ ማታ” የሚል ብሒል ላለው ማህበረሰብ ይሔ ስድብ ነው!!! ያልተፈጠረ አቅም አንደተፈጠረ በፈጠራ ወሬ ማሳመን ሊያውም ሕዝብን አንዲህ ቀላል'ኮ አይደለም፤ የእለት ተለት ኑሮው ምን እንደሚመስል ከህዝቡ በላይ እነእንትና ሊያውቁት አይችሉም፤ መሬት ላይ ያለው ሌላ ነውና፤ አነርሱ ካሉበት የከፍታ ቦታም ሊነፃፀር አይችልም  ምክንያቱም መሬት ላይ አውነት በሽ ነው ከከፍታው ስፍራ ግን ሐሰት ነግሷል! 

የንጉሳዊው ስርዓት ማክተሚያ የነበሩት ንጉስ በጊዜው የተከሰተውን ድርቅና ረሀብ ሸሽገው ለውሻቸው ልደት የ5ሺህ ፓውንድ ኬክ በመቁረስ፣ ከመኳንንትና መሳፍንቶቻቸው ጋር ውሰኪ በመራጨት ትልቁን ታሪካዊ ስህተት ፈፀሙ፤ እርሳቸውን ተከትለው ሀገሪቱን ለመመምራት አራት ኪሎ ቤተመንግሰት የገቡት ወታደሮችም ሕዝቡን ከረሐብና የድርቅ ሰቆቃ ሊታዱጉት አልተቻላቸውም፤ የዛሬዎቹ ደግሞ ጆሮአችን አስኪደማ በውሸት ያደነቁሩናል፣ በዓይናችን የምናየውን ሐቅ ገልብጠው ይነግሩናል፣ የሌለ ነገር አለ ይሉናል!!! አሁንስ ያ ጎበዝ ድምፃዊ አንዳዜመው “ተይ ሀገራችን”  ማለት አሰኘኝ!!!
“ተይ ሀገራችን፤ ተይ ሀገራችን
እናኔ፤ እናኔ፤ እናኔ፤
እናኖ፤ እናኖ፤ እናኖ”

Tuesday, September 22, 2015

“ሂራር!!” አምስተኛው ቅኝት!!

ሳታውቁ በስህተት፤አውቃችሁ በድፍረት እሱ'ኮ መንግስት ሰራተኛ ነው ምትሏት ነገር አትመቸኝም፡፡...እኔ ለሀገር ነው ምሰራ (እንበል አስራ ሁለት ጊዜ)፣መንግስት በሀገር ላይ ነው የሚሰራ (እንበል አስራ ሁለት ጊዜ)...ሁለታችንም እሳት የላስን ንቦች ነን (እንበል አስራ ሁለት ጊዜ)፡፡እኔ ማር ሰራለሁ መንግስት ጠጅ ጥሎ ይጠጣል (እንበል አስራ ሁለት ጊዜ)፣ብርዝ ሰርቶ ይጨልጣል (እንበል አስራ ሁለት ጊዜ)...እኔ የማር እንጀራ ጋግራለሁ እነ እንቶኔ ሰፈፋቸውን ያንሳፍፋሉ...አረ ፍቱን-ወይ ተፋቱን (እንበል አስራ ሁለት ጊዜ)…ሂራራችንን በሰላም አስጀምሮ በሰላም ያስጨርሰን…አሜን!!! 

መንግስት ሀገር አይደለም፣መንግስት መጪና ሂያጅ ነው፣መንግስትነት አላፊ-ጠፊ ነው፡፡ሀገር ግን ዘላለማዊ ናት...እኔ ለሀገር ነው ምሰራ፣በሀገሬ ላይ ነው ምሰራ...የመንግስት ሰራተኛ ብሆን፣ለመንግስት የምሰራ ቢሆን ለምን ከእጅ ወደ አፍ ኑሮ ኖራለሁ?!...ለምን ሿሚ-ተሿሚ አልሆንኩም?!...ለምን የልማት አርበኛ አልተባልኩም?!...ለምን ሞዴል አውርቶ አደር አልተባልኩም?!...ንገሩኛ?!...የምን ስም ለጥፎ ዝም ነው?!...መልሱልኝ እንጂ?!... ለሀገር የሰራ እንጂ የመንግስት ሰራተኛ ታሪክ የለውም ... የመንግስት ሰራተኛ ከመንግስት ጋር ያልፋል፣ለሀገሩ የሚሰራ ግን ከሀገሩ ጋር ዘላለማዊ ሆኖ ይኖራል፡፡ካላጣችሁት ቋንቋ የመንግስት ሰራተኛ የምትሏት መጠሪያ፤ ስንዴውን ከንክርዳዱ ባንድ ቁና መስፈሪያ…ካንድ ስልቻ መክተቻ ተውላጠ ስማችሁ አትመቸኝም፡፡ 

አቦ አትዶክኩና!!... እስቲ እናማርበት?!...እኔ ወር ሙሉ ተጠግርሬ፣ደመወዝ ወጣ አልወጣ ብዬ...ወር ደረስኩ አልደረስኩ ስጋት እያንጠራወዘኝ...ምኑን ከምኑ እንደማረገው ቅጣምባሩ እየጠፋኝ እንደ እርጉዝ ቀን እየቆጠርኩ ከማገኛት አርባ እጅ በላዩን ግብር እያገባሁ ስለምኖር…በዚያ ላይ በአምሮት ነድጄ በምጠጣት ፍልፈል ብርጭቆ ሻይ ሳይቀር አስራ አምስት እጁን በቫት እየተሞጨለፍኩ …ሻይ ሻጩ ነዳጅ ሲጨምር በሚጨምረው፣ሲቀንስ በማይቀንሰው ያንድ ፍልፈል ብርጭቆ ዋጋ ልክ በሁለት ወገን በዱልዱሙ እየተገዘገዝኩ መኖሬ እንደ ውለታ ተቆጥሮ ቢያንስ-ቢያንስ የማማረር የዜግነት መብቴ ይጠበቅልኝ?!... 

ሂራር ህገ መንግስቱን በጉልበት ለመናድ ሙከራ ዝርዝር ውስጥ የለበትም…ህገ መንግስቱ ማንም ሰው ሆኖ የተፈጠረ…በተለይ ኢትዮጲያዊ ሆኖ የተፈጠረ የሚያማርረው ነገር አያጣምና የማማረር ሰብዐዊ መብቱ በህግ ጥበቃና ከለላ ተሰጥቶታል ይላል…ሂራር የማንኛውም ከሀገሩ ሀብት ላይ ተጠቃሚ ያልሆነ ከኑሮ ወለል በታች ያለ ኢትዮጵያዊ ዜጋ የአያልፍልሽ ኑሮ እሮሯዊ ቅኝት ነው…ከፀረ ሰላም ሀይሎች…ከፀረ-ልማት ቡድኞች…አመፅና ሰላማዊ መንገድ እንደ አዋዜ እያጣቀስን እንሄዳለን ከሚሉ ተቃዋሚ የፖለቲካ ፓርቲዎች ተርታ አያስፈርጅም…ሂራር አዲስ አዋጅ በፓርላማ የሚፀድቅበት በቡድን ተግባራዊ ሲሆን ብቻ ነው…

እስከዚያ ድረስ አቦ አትዶክኩና!!... እስቲ እናማርበት?!... አቦ ዝምበሉና የሚሰማን ባይኖርም እናማርበት?!...አዎ እቺ “የመንግስት” ምትለው ቅጥያ ትነሳልንና ለሚገባቸው ለመንግስት አደሮች (ለሆድ አደሮች) ትሁንልን...ቢያንስ-ቢያንስ ያለስማችን አትጥሩን ...የምንሰራው ለሀገር ነው...የሰራንበትን የምትከፍለን ሀገራችን ናት...መንግስት ካሼር ነው፡፡የመንግስት ተቀጣሪነት መንፈሳችን ነው የውድቀታችን ምንጭ፤እቺ ቅጥያችሁ ባመጣችው የፍርሃት ጦስ ነው አዙረው እንደጣሉት ያቴቴ መልከኛ ወሰራ ዶሮ የመንግስት አውደልዳይ አያሌዎች እንደ አሸን የፈላነው… የህሊና እርካታ እንኳ እንዳይኖረን ያደረገን...“የመንግስት” ምትለው ቅጥያ ናት የልግመታችን ፣አውቆ የመተኛት ባህሪያችን መሰረት...ምክንያቱም እኛ ኢትዮጵያውያን ለሀገር የሚሰራ መንግስት አይስጣችሁ…እቺ ሀገር ለወገን አሳቢ ለሀገርና ህዝብ ተቆርቋሪ አይውጣብሽ “ጥቁር ውሻ ውለጂ!!” የሚል እርግማን አለባት መሰለኝ...ለመጪው ትውልድ፣ለታሪክ አስቦ የሚሰራ ቀናዒ ስርዐት አልታደልንም...አልታደለችም፡፡ 

የዚህች አገር መፃኢ ዕድል ቀን ተሌት ሚያባትተው አንድ ወዳጄ የነገረኝን ፤የመንግስት ሰራተኝነት መንፈስ የወለደው በአንድ ክልል መስሪያ ቤት የተፈፀመን ጉድ ላጫውታችሁ...ለኔ የዘመኑ ፖለቲካዊ ስርዐት ፤የኢፍትሐዊነት፣አድሎአዊነት፣ጥቂቶችን ብቻ ተጠቃሚ ያደረገ መንግስታዊ መዋቅር የፈጠረው፤ የአመለካከት ንቅዘት ውጤት ነው ባይ ነኝ...በኤክስፐርቱ፣በምሁርነኝ ባዩ ፤የአንጎል ተከፋይ በሆነው ውቅረኛ ንቀት ሰለባ የሆነው፣ጉልበት ሸጦ ማደር ኩነኔ ሆኖበት የጉልበታሙ በትር ሁሌም የሚያርፍበት “የበታች ሰራተኛው” መደብ ክፍል …ሁሌም የችግሩ ገፈት ቀማሽ የሆነው ሰራተኛ… ያባትህ ቤት ሲዘረፍ አብረህ ዝረፍ ተረት አዳማጭ መሆኑ ሚቆረቁረው…ሲሾም ያልበላ ሲሻር ይቆጨዋል ተረት አራማጅ ሹመኞች የበይ ተመልካች መሆኑ እንቅልፍ የነሳው የሰራተኛ ክፍል… እኔስ ከማን አንሼ ባይነት የተፈፀመ …የመንግስት ሰራተኝነት መንፈስ የወለደው ድርጊት ዛሬ ሀገራዊ አስተሳሰብ ቅኝታችን የት እንደደረሰ ማሳያ ነው ባይ ነኝ… 

ጉዳዩ እንዲህ ነው በዚህ መስሪያ ቤት ለሀገር የሚሰሩ ዜጎች በተለያዩ መንገዶች በደል ይደርስባቸዋል፡፡በብሔራቸውና በፖለቲካ አመለካከታቸው ተገለው የበይ ተመልካች መሆናቸው ሁሌም እንደ እግር እሳት ያንገበግባቸዋል፤ በተለይ ጥጉው ሰራተኛ…ምክንያቱም ወዶም ይሁን ተገዶ፣አሊያም ለመኖር ሲል የሚያፎደፉደው ሰራተኛን አፍ ማዘጊያ ጥቅማ-ጥቅም እንዲያገኝ በስብሰባ፣በስልጠና፣በመስክ ስራ ወዘተ የተጋነነ አበል እንዲያገኝ ይደረጋል...በዚህ አይነት አሰራር …የእከከኝ ልከክህ ሰንሰለት…የበልተህ አብላኝ መዋቅር…እንዳያማህ ጥራው እንዳይበላ ግፋው ፍልስፍና ተጠቂዎች…በዚህ ለመንግስት አደርነት ወረርሽኝ ባመጣው ግለኝነትና ራስወዳድነት ከጥቅም ውጭ የተደረጉት የበታች ሰራተኞች ታዲያ እጃቸውን አጣጥፈው አልተቀመጡም...ሁሉም የድርሻዬን በየት በኩል ልንጠቅ እያለ መላ ይዘይዳል …ሁሉም በቻለው መንገድ ተጠቃሚ ለመሆን ያሴራል…ባገኘው አጋጣሚ የሀገርና ህዝብ ገንዘብ ለመቦጥቦጥ የሚያደባ ተኩላ ጥሩ አድርጎ የሌብነት ሀሁ አስጠንቶታል… በማን ይፈረዳል ነገሩ የአሳ ግማቱ ከወደ አናቱ አይደል…

 የሰው ልጅ መቼም ምንም ቀለም ቢገባውም ባይገባውም…አስኳላ ቢዘልቅም ባይዘልቅም ለተንኮልና ለጥፋት ተፈጥሮው ትበቃዋለች፡፡ ታዲያ በዚህ የመንግስት መስሪያ ቤት የሚገኙት የጥበቃ ሰራተኞች እነሱም የድርሻቸውን ከሀገራቸው ላይ የሚቦጠቡጡበት በር ሁሉ ቢከረቸምባቸው ፊታቸውን በመስሪያቤቱ ውስጥ ወደሚገኙት የሚያማምሩ ዕድሜ ጠገብ ዛፎች ያዞራሉ…ለሊት-ለሊት ጥበቃ ሲያድሩ በማያስነቃ መልኩ ዛፎቹን በቁማቸው እንዲደርቁ ስራቸውን በዘዴ በመበጣጠስ… ላይን በማይታይ ሁኔታ በስለት ግንዳቸውን እየወጉ በማድማት ቀስ በቀስ እንዲደርቁ ያደርጋሉ…በመስሪያ ቤቱ ያልተጻፍ ህግ መሰረት ዛፎች ሲደርቁና ቅርንጫፎቻቸው ሲያስቸግሩ የጥበቃ ሰራተኞች ዛፎቹን ለመቁረጥ የሚያወጡት ጉልበት ታሳቢ ተደርጎ ካትክልተኞች ጋር የማገዶ ቅርጫ እንዲገቡ ማድረግ የተለመደ ነው፡፡ ይሄ ባብዛኛው አለቃ ዘንድ የበታች ሰራተኞችን እንደ አፍ ማዘጊያ ጥቅማጥቅምም የሚቆጠር ነው…አንዳንዴም ደፈር ያለ የጥበቃ ሰራተኛ ሲመጣ ከዚህ በኋላ ማገዶውን በጨረታ እንሸጠዋለን እያሉም ያስቦካኩበታል …አንዳንድ በጠመንጃ የሚጠበቅ የመንግስት መስሪያ ቤት ጥበቆች ከአለቆቻቸው ጋር ሲዋገሙ “እኔ የከፋኝ ሰው ነኝ ደፍቼው እጄን ለመንግስት ሰጣለሁ” እያሉ ስለሚዝቱ ማገዶው አትወስድም ማለት ለአብዛኛው ሹመኛ የማይሞከር ነው… 

ታዲያ ዛፍ ከደረቀ በኋላ ባለቅርጫዎቹ በፊርማቸው የተስማሙበት በግቢው ውስጥ ያለውን የደረቀ ዛፍ (ምክንያቱ አይጠቀስም)ቆርጠን እንውሰድ ጥያቄ የያዘ ደብዳቤ በጥበቃ ጓድ መሪያቸው አማካኝነት ለአለቃው ይቀርባል፡፡ለተፈፃሚነቱ የአለቃው ትዕዛዝ ተዋረዱን ጠብቆ፣የስልጣን ሰንሰለቱን ማዕከል አድርጎ …ህጋዊ መሰረት እንዲይዝ ተደርጎ የማገዶ ቅርጫ ክፍፍሉ ተግባራዊ ይደረጋል …በዚህም ሰራተኞቹ ከሀገራቸው ሀብት ላይ የበኩላቸውን ተጠቃሚነት ያረጋግጣሉ፡፡ ይኼ ባንድ መስሪያ ቤት ውስጥ እየተፈፀመ ያለ ድርጊት መልክና ቅርፁን ቀይሮ በሌሎችም ቦታዎች ስላለመደረጉ ዋስትና የለንም፡፡ ምክንያቱም በዚህ ሴራ፣በዚህ የነቀዘ አመለካከት፣በዚህ እኔ ከሞትኩ ሰርዶ አይብቀል አህያዊ አስተሳሰብ የመንግስት ሰራተኛው ከትልቅ እስከ ትንሹ እየቦካ ስለመምጣቱ ይኼ የድንቁርና ድርጊት አመላካች ነው፡፡

 መንግስት ሰራተኝነት የወለደው፣የወቅቱ ስርዐትና ፖለቲካ የፈጠረው የመልካም አስተዳደር ችግር ሀገራዊ አመለካከት ዋግ እየመታው፣ኢትዮጵያዊነት ዛሬ በልቼ ልሙት በሚል ማህበረሰባዊ ቅኝት እየተቃኘ ስለመምጣቱ፣ ስርዐት ወለድ ያመለካከት ተስቦ ወረርሽኝ ምልክት ነው፡፡ይኽ ነቀርሳዊ አመለካከት ከቤተሰብ ወደ ልጅ፣ካንድ መንደር ወደ ሌላ መንደር፣ካንዱ ክልል ወደሌላው ክልል እየተዛመተ ነገ ሀገር የሚያጠፋ ሰደድ እሳት መሆኑም አይቀርም…እየሆነም ነው፡፡

…ይኼም ሂራር ነው…ስድስተኛው እሮሯዊ ሀገርኛ ኑሮ የወለደው ሙዚቃዊ ቅኝት!! ሳታውቁ በስህተት፤አውቃችሁ በድፍረት እሱ'ኮ መንግስት ሰራተኛ ነው ምትሏት ነገር ማትመቸኝ የዚህ አመለካከት ዕድርተኞች፣ዕቁብተኞች፣ባለደቦዎች ባለወንፈሎች ጋር የምታወናፍል… ከኑግ ጋር የተገኘህ ሰሊጥ አብረህ ተወቀጥ አይነት…ጅብ በበላ ዳዋ ተመታ አይነት ጅምላ ፍረጃ ብትሆንብኝ ነው…...ለምን ቢባል የመንግስት ሰራተኛ ከመንግስት ጋር ያልፋል፣ለሀገሩ የሚሰራ ግን ከሀገሩ ጋር ዘላለማዊ ሆኖ ይኖራል፡፡ካላጣችሁት ቋንቋ የመንግስት ሰራተኛ ምትሏት መጥሪያችሁ ስንዴውን ከንክርዳዱ ባንድ ቁና መስፈሪያ…ካንድ ስልቻ መክተቻ የተውላጠ ስም ታርጋችሁ በ“ሀ.ሰ.” ትተካልኝ፡፡ሂራራችንን በሰላም አስጀምሮ በሰላም ያስጨረሰን ሕገ-መንግስታችን ስሙ ይባረክ!!… በግራችሁ ለሂራር እንደመጣችሁ በባቡር ወደ ቤታችሁ ተመለሱ…አሜን!!!

Saturday, September 19, 2015

አንጀት የሚበላ ሀባሻዊ አንጀት!!



ሀበሻነቴን ያለቅጥ እወደዋለሁ፡፡ኢትዮጵያዊነቴን የምወደው ማንነቴ ብቻ ሳይሆን መደነቂያዬ፣የአግራሞቴ ምንጭ፣የመደነቅ ጥበብ ያወረሰኝ ስጦታዬ ስለሆነም ጭምር ነው፡፡ሀበሻና ሀበሻዊነት ለእንደኔ አይነቱ ለአድናቂና ተደናቂ የእውቀት፣የጥበብ፣የትዝብት፣የፌዝና የሳቅ መፍለቂያ ከመሆን በላይ ሰርክ በአድናቆት የሚወዘውዝ ሀበሻዊ መልክ፣ኢትዮጵያዊ ገፅ እና ቀለም ጋር ባንድነት ከሌላው ዓለም ሰዎች በተለየ ሁናቴ በኢትዮጵያዊ ማንነትና ሰውነት ተውቦና ተኩሎ የሚገኝባት በዚህችው እኔኑ መሽቶ በነጋ ቁጥር በምታስደምመኝ... ለድማሜ በተፈጠርኩባት፣በፈጠረችኝ ሀገር እና ወገን መሀል ስላለሁ  ይመስለኛል፡፡

የሀገሬ ሰው ብዙ ነገሩ ድንቅ ይለኛል...አንዳንዴ እግዜሩ እኔን ብቻ ነው እንዴ በትንሽ-በትልቁ፣በረባው ባልረባው አስገራሚ ሳይሆን ተገራሚ አድርጎ የፈጠረኝ እያልኩ እገረማለሁ...ሁሌም  ዓውደ-ዓመት በመጣ ቁጥር አግራሞቴን የሚጭረው ጉዳይ አንጀት የሚበላው ሀበሻዊ አንጀታችን ነው፡፡ሀበሻና አንጀት ያላቸው ትውፊታዊ፣ስነልቦናዊ ቁርኝት ከመደነቂያ ሀበሻዊ ጉዳዮቼ አንደኛው ነው፡፡ መደነቄ ቅጥ እና ወደር የለውም የምላችሁ ከልቤ ስለሚያስደንቀኝ ነው፡፡ለምን ቢሉ በምድራችን ላይ አንጀት የሚበላ፤አንጀቱም የሚበላ ህዝብ ኢትዮጵያዊ ብቻ ይመስለኛል፡፡እንዴት?!...ለምን ካላችሁ?!...ይኸው አስረጂ
               በላሽው አንጀቴን በላሽው
               በላሽው አንጀቴን በላሽው
               ሸገር አዲሳባ ሸዋ ላይ ያለሽው
እያለ በዘፈንና፣በግጥም አንጀት የሚበላና፣አንጀቱ የሚበላ ህዝብ በሌላው ዓለም ስለመኖሩ እጠራጠራለሁ፡፡ለአንጀት ልዩ ፍቅር አለው ህዝቤ፣...ለአንጀት ልዩ ስፍራ አለው ያገሬ ሰው፣...አንጀት ቅኔው፣አንጀት ሰምና ወርቁ ነው ወገኔ...አንጀት መለያው፣አንጀቱ መታወቂያው ነው ሀበሻ...ባንጀት እና ባንጀቱ ፌዝ አያውቅም...ሀበሻን ባንጀትና በሆዱ አትምጡበት...ከመጣችሁበት ግን...
               አንጀቴና ሆዴ ተጣልተውብኝ
               አንተም ተው ፣አንተም ተው እንዳልላቸው
               አንጀቴም አንጀቴ፤ሆዴም-ሆዴ ነው
ይላችኋል፡፡
ሀበሻ አንጀት ሲበላ አልቦ ነው የሚበላ...አንጀት ገምዶ፣ፈትሎ ነው የሚበላ...አንጀት አድቅቆ ነው የሚበላ...የሚበላው የሰው አንጀት ቢያጣ የከብት አንጀት በፍቅር ይበላል ያገሬ ሰው፡፡በልዩ ሀበሻዊ ጥበብ እና ብልሃቱ በቅመም አሳብዶ በቃሪያ፣በጥብስ ቅጠል፣በነጭ ሽንኩርት አቁላልቶ፣ዶልቶ...ዱለት አርጎ...አንጀት ጠብሶ፣አንጀት ለብለብ አርጎ አሊያም በጥሬው አንጀት ይበላል ኢትዮጵያዊ፡፡

ያገሬ ሰው አንጀት መብላት ያውቅበታል፡፡ሀበሻ በግ የሚያርደው ለዱለት ካለው ጥልቅ ፍቅር የተነሳ ይመስለኛል፡፡አንጀት ለመብላት ይመስለኛል፡፡ሀበሻ ዱለት ማልዶ ሳይቀምስ ቅልጥም አይቀለጥምም፣ፍሪምባና ጎድን፣ሳላይሰጥና ወርች አያምረውም፡፡ዱለት ዓውደ-ዓመት ማድመቀዊያው ነው፤...ሀበሻ በዓል-በዓል የሚሸተው የትኩስ ዱለት መዓዛ አፍንጫውን ሲኮረኩረው፣ሰርኑን ሰርስሮ ሲገባ ነው፡፡የዱለት መዓዛ ከጠጅ-ሳር፣አሪቲ፣ጤናዳም፣ከከርቤና እጣን ጢስ፣ከጠጅና ጠላው፣ከቁሌት ጋር የተደባልቆ  አየሩን ሲሞላው...ይኼን ዱለታዊ የማለዳ አየር ማግ-ማግ ሲያደርግ ነው ዓውዳመቱ ዓውዳመት የሚመ ስለው...በዓሉ በዓል የሚሆንለት፡፡
ለሀበሻ ዱለት የሌለበት በዓል ትዝታ የለውም፣ጎደሎ ነው፡፡...አንጀት የሚያቃጥል፣አንጀት የሚለበልብ፣አንጀት የሚያነድ ዓውዳመታዊ ጠባሳ ጥሎበት ያልፋል፡፡ሀበሻ በዓል፣ድግስ፣ሰርግና ተዝካር የማይለየው አንጀት ለመብላት ይመስለኛል፡፡ለዚህ ነው ኢትዮጲያውነቴ አንጀቴን የሚበላው፣አንጀቴን የሚያንሰፈስፈው፡፡

ሀበሻ ክፉ ቀኑን የሚችለው፣መከራና ስቃዩን፣በደል እና ጭቆናውን፣የመገፋት ቁጭቱን የሚያዳፍነው አንጀቱ ስር ነው፣ካንጀቱ ቀብሮ ነው፤ ባገሬ ሁሉን ቻይ አንጀት ያለው ሰው ይቀናበታል፡፡ያገሬ ሰው ሲኩራራ የዝሆን አንጀት ሰጥቶኛል ይላል፤ክፉና በጎውን እንዳመጣጡ የሚቀበልበት ሰፊ ሆድ እና ባለገበር አንጀት የሰጠውን ፈጣሪውን ተመስገን ብሎ የባሰ አታምጣ እያለ የሚኖረው ባንጀቱ ድንዳኔ እና ክሳት ልክ ነው ብሎ ያምናል፡፡ላበሻ ረጅሙ አንጀቱ የኑሮ ማሳለጫው፣ከክፉ ቀን መሰወሪያው ፣መሸሸጊያው ነው፡፡

ወገኔ የነገር መክተቻ ስልቻው፣እውነተኛ ስሜቱን መደበቂያ ጎተራው፣ክፉና ደጉን ማጎሪያ ጉረኖው አንጀቱ ነው፡፡ያገሬ ሰው የልቡን-በልቡ ያንጀቱንም-ባንጀቱ መያዝ የተካነ ዚቀኛ ነው፡፡እንኳን ለባዳ ለወዳጁም ያንጀቱን አያወጣም፣መዋደድ እንዳለ መጣላት ይመጣል ብሎ አርቆ አስቦ አንጀቱን ያርቃል፡፡ሀበሻ ሀዘን ደጁን ረግጦ፣ከቤቱ አልወጣ ቢለው...ልብና አንጀቱን ጠብስቆ ሲያብሰከስከው አንጀቴ ተላወሰ፣አንጀቴ ተንሰፈሰፈ፣አንጀቴን በላኝ ይላል የሀዘኑን ጥግ ሊገልፅ ሲፈልግ፡፡

ሀበሻ ያመነው ሲከዳው፣ወዳጄ ያለው ፊቱን ሲያዞርበት፣የኔ የሚለው ሰው ቃሉን በልቶ፣እምነቱን አጉድሎ ፣ማተቡን በጥሶ ዋሾና ቀጣፊ ሆኖ ሲያገኘው አንጀቴ ተቆረጠ፣አንጀቴ ተበጠሰ ብሎ ቅያሜውን የሚገልፀው አንጀቱን ምሳሌ አርጎ አንጀቱን ተውሶ ነው፡፡

የሀበሻ ሰው ፍቅሩ እንጂ መቼም ጠቡ አያድርስ ነው፡፡ሀበሻ መውደዱ እንጂ ጥላቻው ለጉድ ነው፡፡ሀበሻ ያቄመ እንደሁ አይጣል ነው፡፡ሀበሻ እንኳን ቂም እና ጥላቻውን ፍቅሩን መሰወሪያ ስልቻው አንጀቱ ነው፡፡ሀበሻ አንጀቱ ዋሻው ነው፡፡አንጀቱ ራስ መደበቂያው አመሉን መክተቻ አቁማዳው ነው፡፡ሀበሻ ነገር ማሰንበቻ፣ማኮምጠጪያ፣ማርጊያ አካሌ አንጀቴ ነው ይላል...ነገር ሲገባው ተው ቻለው አንጀቴን ማንጎራጎር ልማድ አለው፡፡ሀበሻ ፍቅርና ደግነቱን፣የክፋትና ጥላቻ አብሲቱን የሚጥለው፣የሚያብላላው፣የሚደፈድፈው፣የሚያፈላው ፣የሚያቀዘቅዘው ባንጀቱ ውስጥ ነው፡፡

ሀበሻ እንኳን ለወዳጁ ለራሱም ስውር ነው፡፡ወሬና ነገር ከሆዱ ማይረጋለት፣ካንጀቱ ማይቀመጥለት ሀበሻ ነውረኛ ፣ምስጢር መቋጠሪያ የሌለው ወሽካታ፣ወናፍ፣አንድ አይውል፣ ቁምነገረ-ቢስ፣ ከንቱ ተደርጎ ይብጠለጠላል፡፡ሀበሻ አንጀተ ደንዳና እንጂ አንጀተ ወንዋና፣አንጀተ ከሲታ ጥሎበት አይወድም፡፡አንጀተ ልፍስፍስ ሰው ጀግና፣ደፋር፣ጎበዝ፣ብርቱ ከሚውልበት አደባባይ አይውልም፤ ካንድ ማዕድ አይቆርስም፡፡
ሀበሻ  ደስ ሲለው፣የልቡ ሲደርስ፣ያሰበው ሲሳካለት፣የተመኘው ሲሆንለት፣ስለቱ ሲሰምርለት አንጀቴ ቂቤ ጠጣ፣አንጀቴ ራሰ ብሎ የደስታ ጥሙን የሚቆርጠው፣የእርካታ ፅዋውን የሚጨልጠው ወደ አንጀቱ ነው፡፡

ታዲያስ እኔስ ሀበሻ አይደለሁ አንጀት መብላት የለመደ ሀበሻዊ አንጀቴ አውደ-ዓመት ሲመጣ ናድ-ናድ ፣ፍርስ-ፍርስ ይልብኛል...የዘንድሮው በአል  ደግሞ ባዲስ ህዳሴያዊ ፍቅር አንጀቴን ያንሰፈስፈው ይዟል!...ተሳለጥ-ተሳለጥ ይለኛልጂቲፒ-ጂቲፒ ይለኛልተናገር-ተናገር ይለኛልቃሊቲ-ቃሊቲ ይለኛልጉባዔ-ጉባዔ ይለኛል….እንብላ-እንብላ ይለኛልእሰር-እሰር ይለኛልአሸባሪ-አሸባሪ እያለ ሽብር ይለቅብኛልፍትህ-ፍትህ ይለኛልተሰደድ-ተሰደድ ይለኛልሀገር የለህም ይለኛልአንጀቴ ስሩ ይመረኛልእልህ አንጀቴን ያስልበኛልያልሄድንበት መንገድ ጨኛልየምናወራውና ተግባራችን ፍየል ወዲህ ቅዝምዝም ወዲያ ይሆንብኛልአረ አይነጋም ወይ ያስቀነቅነኛልየጨለማ ጉዟችን ማብቂያ አልታይህ ይለኛልበመርከባችን ካፒቴኖች እንደ ውሃ ላይ ኩበት መዋለል ታክቶኛልአርበኝነት እየከሰመ ሞላጫነት እየነገሰ ሲመጣ እያየሁ የተስፋ አንጀት ርቆኛልየሚያዋጣኝ ይሄን እሳትራታዊ ሃሳብ ወዲያ ትቶ አረ-ምኑን ሰጠሽ እያልኩ መዝፈንአሊያም በዚህ አዲስ ዓመት ከቀናኝ አንድ ምኑ የተሰጣትን ባለመቀመጫ ፈልጌ ከጢዟ ስር ተደብቄ ይሄን ክፉ ቀን ማሳለፍ
ለናንተ ለወገኖቼ አውደ-ዓመት ሲመጣ የዱለት አምሮት የጠናበት፤ ሀበሻዊ ሆድና አንጀታችሁ ለሚባባ ከሀገር እና ቤተሰብ ርቃቸሁ፣የስደት ኑሮ፣የባዕድ ሀገር ህይወት አልሞላ ላላችሁ መለየትና ናፍቆት አንጀታችሁን ለሚበላችሁ፣...እናት እና አባታችሁን፣ባልና ሚስታችሁን፣ወንድምና እህታችሁን፣ፍቅረኛና ልጃችሁን ሞት ቀምቶ ሀዘን አንጀታችሁን ለሚያኝከው፣...በዘመኑ ፖለቲካ ያለወንጀላችሁ ከእስርቤት ተወርውራችሁ፣ዘብጢያ ወርዳችሁ በክፋት ጓጉንቸር ለተከረቸማችሁ፣በሆስፒታል አልጋ ላይ በህመምና  በስቃይ ላላችሁ፣ የምትወዷት ወይም የምትወዱት ልጅ ቤተሰብ ጥየቃ ሄዶባችሁ በመለየትና በብቸኝነት አንጀታችሁ ለሚላወስ እና ዱለት አልበላ ላላችሁ፣ለከፋችሁም-ደስ ላላችሁም፣ለሞላላችሁም-ለጎደለባችሁም...ለትንሾቹም ለትልቆቹም...ለእናንተ ለወገኖቼ ለሁላችሁ አንጀት ሚወደው፣ዱለት ያማረው ሀበሻዊ አንጀቴ እስኪላወስ እወዳችኋለው...መልካም አዲስ-ዓመት ይሁንላችሁ፡፡