Tuesday, September 22, 2015

“ሂራር!!” አምስተኛው ቅኝት!!

ሳታውቁ በስህተት፤አውቃችሁ በድፍረት እሱ'ኮ መንግስት ሰራተኛ ነው ምትሏት ነገር አትመቸኝም፡፡...እኔ ለሀገር ነው ምሰራ (እንበል አስራ ሁለት ጊዜ)፣መንግስት በሀገር ላይ ነው የሚሰራ (እንበል አስራ ሁለት ጊዜ)...ሁለታችንም እሳት የላስን ንቦች ነን (እንበል አስራ ሁለት ጊዜ)፡፡እኔ ማር ሰራለሁ መንግስት ጠጅ ጥሎ ይጠጣል (እንበል አስራ ሁለት ጊዜ)፣ብርዝ ሰርቶ ይጨልጣል (እንበል አስራ ሁለት ጊዜ)...እኔ የማር እንጀራ ጋግራለሁ እነ እንቶኔ ሰፈፋቸውን ያንሳፍፋሉ...አረ ፍቱን-ወይ ተፋቱን (እንበል አስራ ሁለት ጊዜ)…ሂራራችንን በሰላም አስጀምሮ በሰላም ያስጨርሰን…አሜን!!! 

መንግስት ሀገር አይደለም፣መንግስት መጪና ሂያጅ ነው፣መንግስትነት አላፊ-ጠፊ ነው፡፡ሀገር ግን ዘላለማዊ ናት...እኔ ለሀገር ነው ምሰራ፣በሀገሬ ላይ ነው ምሰራ...የመንግስት ሰራተኛ ብሆን፣ለመንግስት የምሰራ ቢሆን ለምን ከእጅ ወደ አፍ ኑሮ ኖራለሁ?!...ለምን ሿሚ-ተሿሚ አልሆንኩም?!...ለምን የልማት አርበኛ አልተባልኩም?!...ለምን ሞዴል አውርቶ አደር አልተባልኩም?!...ንገሩኛ?!...የምን ስም ለጥፎ ዝም ነው?!...መልሱልኝ እንጂ?!... ለሀገር የሰራ እንጂ የመንግስት ሰራተኛ ታሪክ የለውም ... የመንግስት ሰራተኛ ከመንግስት ጋር ያልፋል፣ለሀገሩ የሚሰራ ግን ከሀገሩ ጋር ዘላለማዊ ሆኖ ይኖራል፡፡ካላጣችሁት ቋንቋ የመንግስት ሰራተኛ የምትሏት መጠሪያ፤ ስንዴውን ከንክርዳዱ ባንድ ቁና መስፈሪያ…ካንድ ስልቻ መክተቻ ተውላጠ ስማችሁ አትመቸኝም፡፡ 

አቦ አትዶክኩና!!... እስቲ እናማርበት?!...እኔ ወር ሙሉ ተጠግርሬ፣ደመወዝ ወጣ አልወጣ ብዬ...ወር ደረስኩ አልደረስኩ ስጋት እያንጠራወዘኝ...ምኑን ከምኑ እንደማረገው ቅጣምባሩ እየጠፋኝ እንደ እርጉዝ ቀን እየቆጠርኩ ከማገኛት አርባ እጅ በላዩን ግብር እያገባሁ ስለምኖር…በዚያ ላይ በአምሮት ነድጄ በምጠጣት ፍልፈል ብርጭቆ ሻይ ሳይቀር አስራ አምስት እጁን በቫት እየተሞጨለፍኩ …ሻይ ሻጩ ነዳጅ ሲጨምር በሚጨምረው፣ሲቀንስ በማይቀንሰው ያንድ ፍልፈል ብርጭቆ ዋጋ ልክ በሁለት ወገን በዱልዱሙ እየተገዘገዝኩ መኖሬ እንደ ውለታ ተቆጥሮ ቢያንስ-ቢያንስ የማማረር የዜግነት መብቴ ይጠበቅልኝ?!... 

ሂራር ህገ መንግስቱን በጉልበት ለመናድ ሙከራ ዝርዝር ውስጥ የለበትም…ህገ መንግስቱ ማንም ሰው ሆኖ የተፈጠረ…በተለይ ኢትዮጲያዊ ሆኖ የተፈጠረ የሚያማርረው ነገር አያጣምና የማማረር ሰብዐዊ መብቱ በህግ ጥበቃና ከለላ ተሰጥቶታል ይላል…ሂራር የማንኛውም ከሀገሩ ሀብት ላይ ተጠቃሚ ያልሆነ ከኑሮ ወለል በታች ያለ ኢትዮጵያዊ ዜጋ የአያልፍልሽ ኑሮ እሮሯዊ ቅኝት ነው…ከፀረ ሰላም ሀይሎች…ከፀረ-ልማት ቡድኞች…አመፅና ሰላማዊ መንገድ እንደ አዋዜ እያጣቀስን እንሄዳለን ከሚሉ ተቃዋሚ የፖለቲካ ፓርቲዎች ተርታ አያስፈርጅም…ሂራር አዲስ አዋጅ በፓርላማ የሚፀድቅበት በቡድን ተግባራዊ ሲሆን ብቻ ነው…

እስከዚያ ድረስ አቦ አትዶክኩና!!... እስቲ እናማርበት?!... አቦ ዝምበሉና የሚሰማን ባይኖርም እናማርበት?!...አዎ እቺ “የመንግስት” ምትለው ቅጥያ ትነሳልንና ለሚገባቸው ለመንግስት አደሮች (ለሆድ አደሮች) ትሁንልን...ቢያንስ-ቢያንስ ያለስማችን አትጥሩን ...የምንሰራው ለሀገር ነው...የሰራንበትን የምትከፍለን ሀገራችን ናት...መንግስት ካሼር ነው፡፡የመንግስት ተቀጣሪነት መንፈሳችን ነው የውድቀታችን ምንጭ፤እቺ ቅጥያችሁ ባመጣችው የፍርሃት ጦስ ነው አዙረው እንደጣሉት ያቴቴ መልከኛ ወሰራ ዶሮ የመንግስት አውደልዳይ አያሌዎች እንደ አሸን የፈላነው… የህሊና እርካታ እንኳ እንዳይኖረን ያደረገን...“የመንግስት” ምትለው ቅጥያ ናት የልግመታችን ፣አውቆ የመተኛት ባህሪያችን መሰረት...ምክንያቱም እኛ ኢትዮጵያውያን ለሀገር የሚሰራ መንግስት አይስጣችሁ…እቺ ሀገር ለወገን አሳቢ ለሀገርና ህዝብ ተቆርቋሪ አይውጣብሽ “ጥቁር ውሻ ውለጂ!!” የሚል እርግማን አለባት መሰለኝ...ለመጪው ትውልድ፣ለታሪክ አስቦ የሚሰራ ቀናዒ ስርዐት አልታደልንም...አልታደለችም፡፡ 

የዚህች አገር መፃኢ ዕድል ቀን ተሌት ሚያባትተው አንድ ወዳጄ የነገረኝን ፤የመንግስት ሰራተኝነት መንፈስ የወለደው በአንድ ክልል መስሪያ ቤት የተፈፀመን ጉድ ላጫውታችሁ...ለኔ የዘመኑ ፖለቲካዊ ስርዐት ፤የኢፍትሐዊነት፣አድሎአዊነት፣ጥቂቶችን ብቻ ተጠቃሚ ያደረገ መንግስታዊ መዋቅር የፈጠረው፤ የአመለካከት ንቅዘት ውጤት ነው ባይ ነኝ...በኤክስፐርቱ፣በምሁርነኝ ባዩ ፤የአንጎል ተከፋይ በሆነው ውቅረኛ ንቀት ሰለባ የሆነው፣ጉልበት ሸጦ ማደር ኩነኔ ሆኖበት የጉልበታሙ በትር ሁሌም የሚያርፍበት “የበታች ሰራተኛው” መደብ ክፍል …ሁሌም የችግሩ ገፈት ቀማሽ የሆነው ሰራተኛ… ያባትህ ቤት ሲዘረፍ አብረህ ዝረፍ ተረት አዳማጭ መሆኑ ሚቆረቁረው…ሲሾም ያልበላ ሲሻር ይቆጨዋል ተረት አራማጅ ሹመኞች የበይ ተመልካች መሆኑ እንቅልፍ የነሳው የሰራተኛ ክፍል… እኔስ ከማን አንሼ ባይነት የተፈፀመ …የመንግስት ሰራተኝነት መንፈስ የወለደው ድርጊት ዛሬ ሀገራዊ አስተሳሰብ ቅኝታችን የት እንደደረሰ ማሳያ ነው ባይ ነኝ… 

ጉዳዩ እንዲህ ነው በዚህ መስሪያ ቤት ለሀገር የሚሰሩ ዜጎች በተለያዩ መንገዶች በደል ይደርስባቸዋል፡፡በብሔራቸውና በፖለቲካ አመለካከታቸው ተገለው የበይ ተመልካች መሆናቸው ሁሌም እንደ እግር እሳት ያንገበግባቸዋል፤ በተለይ ጥጉው ሰራተኛ…ምክንያቱም ወዶም ይሁን ተገዶ፣አሊያም ለመኖር ሲል የሚያፎደፉደው ሰራተኛን አፍ ማዘጊያ ጥቅማ-ጥቅም እንዲያገኝ በስብሰባ፣በስልጠና፣በመስክ ስራ ወዘተ የተጋነነ አበል እንዲያገኝ ይደረጋል...በዚህ አይነት አሰራር …የእከከኝ ልከክህ ሰንሰለት…የበልተህ አብላኝ መዋቅር…እንዳያማህ ጥራው እንዳይበላ ግፋው ፍልስፍና ተጠቂዎች…በዚህ ለመንግስት አደርነት ወረርሽኝ ባመጣው ግለኝነትና ራስወዳድነት ከጥቅም ውጭ የተደረጉት የበታች ሰራተኞች ታዲያ እጃቸውን አጣጥፈው አልተቀመጡም...ሁሉም የድርሻዬን በየት በኩል ልንጠቅ እያለ መላ ይዘይዳል …ሁሉም በቻለው መንገድ ተጠቃሚ ለመሆን ያሴራል…ባገኘው አጋጣሚ የሀገርና ህዝብ ገንዘብ ለመቦጥቦጥ የሚያደባ ተኩላ ጥሩ አድርጎ የሌብነት ሀሁ አስጠንቶታል… በማን ይፈረዳል ነገሩ የአሳ ግማቱ ከወደ አናቱ አይደል…

 የሰው ልጅ መቼም ምንም ቀለም ቢገባውም ባይገባውም…አስኳላ ቢዘልቅም ባይዘልቅም ለተንኮልና ለጥፋት ተፈጥሮው ትበቃዋለች፡፡ ታዲያ በዚህ የመንግስት መስሪያ ቤት የሚገኙት የጥበቃ ሰራተኞች እነሱም የድርሻቸውን ከሀገራቸው ላይ የሚቦጠቡጡበት በር ሁሉ ቢከረቸምባቸው ፊታቸውን በመስሪያቤቱ ውስጥ ወደሚገኙት የሚያማምሩ ዕድሜ ጠገብ ዛፎች ያዞራሉ…ለሊት-ለሊት ጥበቃ ሲያድሩ በማያስነቃ መልኩ ዛፎቹን በቁማቸው እንዲደርቁ ስራቸውን በዘዴ በመበጣጠስ… ላይን በማይታይ ሁኔታ በስለት ግንዳቸውን እየወጉ በማድማት ቀስ በቀስ እንዲደርቁ ያደርጋሉ…በመስሪያ ቤቱ ያልተጻፍ ህግ መሰረት ዛፎች ሲደርቁና ቅርንጫፎቻቸው ሲያስቸግሩ የጥበቃ ሰራተኞች ዛፎቹን ለመቁረጥ የሚያወጡት ጉልበት ታሳቢ ተደርጎ ካትክልተኞች ጋር የማገዶ ቅርጫ እንዲገቡ ማድረግ የተለመደ ነው፡፡ ይሄ ባብዛኛው አለቃ ዘንድ የበታች ሰራተኞችን እንደ አፍ ማዘጊያ ጥቅማጥቅምም የሚቆጠር ነው…አንዳንዴም ደፈር ያለ የጥበቃ ሰራተኛ ሲመጣ ከዚህ በኋላ ማገዶውን በጨረታ እንሸጠዋለን እያሉም ያስቦካኩበታል …አንዳንድ በጠመንጃ የሚጠበቅ የመንግስት መስሪያ ቤት ጥበቆች ከአለቆቻቸው ጋር ሲዋገሙ “እኔ የከፋኝ ሰው ነኝ ደፍቼው እጄን ለመንግስት ሰጣለሁ” እያሉ ስለሚዝቱ ማገዶው አትወስድም ማለት ለአብዛኛው ሹመኛ የማይሞከር ነው… 

ታዲያ ዛፍ ከደረቀ በኋላ ባለቅርጫዎቹ በፊርማቸው የተስማሙበት በግቢው ውስጥ ያለውን የደረቀ ዛፍ (ምክንያቱ አይጠቀስም)ቆርጠን እንውሰድ ጥያቄ የያዘ ደብዳቤ በጥበቃ ጓድ መሪያቸው አማካኝነት ለአለቃው ይቀርባል፡፡ለተፈፃሚነቱ የአለቃው ትዕዛዝ ተዋረዱን ጠብቆ፣የስልጣን ሰንሰለቱን ማዕከል አድርጎ …ህጋዊ መሰረት እንዲይዝ ተደርጎ የማገዶ ቅርጫ ክፍፍሉ ተግባራዊ ይደረጋል …በዚህም ሰራተኞቹ ከሀገራቸው ሀብት ላይ የበኩላቸውን ተጠቃሚነት ያረጋግጣሉ፡፡ ይኼ ባንድ መስሪያ ቤት ውስጥ እየተፈፀመ ያለ ድርጊት መልክና ቅርፁን ቀይሮ በሌሎችም ቦታዎች ስላለመደረጉ ዋስትና የለንም፡፡ ምክንያቱም በዚህ ሴራ፣በዚህ የነቀዘ አመለካከት፣በዚህ እኔ ከሞትኩ ሰርዶ አይብቀል አህያዊ አስተሳሰብ የመንግስት ሰራተኛው ከትልቅ እስከ ትንሹ እየቦካ ስለመምጣቱ ይኼ የድንቁርና ድርጊት አመላካች ነው፡፡

 መንግስት ሰራተኝነት የወለደው፣የወቅቱ ስርዐትና ፖለቲካ የፈጠረው የመልካም አስተዳደር ችግር ሀገራዊ አመለካከት ዋግ እየመታው፣ኢትዮጵያዊነት ዛሬ በልቼ ልሙት በሚል ማህበረሰባዊ ቅኝት እየተቃኘ ስለመምጣቱ፣ ስርዐት ወለድ ያመለካከት ተስቦ ወረርሽኝ ምልክት ነው፡፡ይኽ ነቀርሳዊ አመለካከት ከቤተሰብ ወደ ልጅ፣ካንድ መንደር ወደ ሌላ መንደር፣ካንዱ ክልል ወደሌላው ክልል እየተዛመተ ነገ ሀገር የሚያጠፋ ሰደድ እሳት መሆኑም አይቀርም…እየሆነም ነው፡፡

…ይኼም ሂራር ነው…ስድስተኛው እሮሯዊ ሀገርኛ ኑሮ የወለደው ሙዚቃዊ ቅኝት!! ሳታውቁ በስህተት፤አውቃችሁ በድፍረት እሱ'ኮ መንግስት ሰራተኛ ነው ምትሏት ነገር ማትመቸኝ የዚህ አመለካከት ዕድርተኞች፣ዕቁብተኞች፣ባለደቦዎች ባለወንፈሎች ጋር የምታወናፍል… ከኑግ ጋር የተገኘህ ሰሊጥ አብረህ ተወቀጥ አይነት…ጅብ በበላ ዳዋ ተመታ አይነት ጅምላ ፍረጃ ብትሆንብኝ ነው…...ለምን ቢባል የመንግስት ሰራተኛ ከመንግስት ጋር ያልፋል፣ለሀገሩ የሚሰራ ግን ከሀገሩ ጋር ዘላለማዊ ሆኖ ይኖራል፡፡ካላጣችሁት ቋንቋ የመንግስት ሰራተኛ ምትሏት መጥሪያችሁ ስንዴውን ከንክርዳዱ ባንድ ቁና መስፈሪያ…ካንድ ስልቻ መክተቻ የተውላጠ ስም ታርጋችሁ በ“ሀ.ሰ.” ትተካልኝ፡፡ሂራራችንን በሰላም አስጀምሮ በሰላም ያስጨረሰን ሕገ-መንግስታችን ስሙ ይባረክ!!… በግራችሁ ለሂራር እንደመጣችሁ በባቡር ወደ ቤታችሁ ተመለሱ…አሜን!!!

0 comments