Monday, November 9, 2015

ያንድ ሰንጋ ትርጉም በሁለት ልኳንዳ ቤቶች ካራ

.
ይኽ በስዕሉ ላይ የምትመለከቱት የስጋ ተራራ የተሰኘ ሰንጋ የትውልድ መንደሩ ከወደ ሐረር ነው፡፡ አሳዳጊው ሐረር ውስጥ የምትገኝ አንድ የገጠር ቀበሌ መስጂድ ሼህ የሆኑት ሀጂ እንድሪስ ናቸው፡፡የዚህ መልከኛ ሻኛም ሰንጋ የዘር ሀረግ ሲመዘዝ እንደሚከተለው ነው፡፡የእናቱ የትውልድ ሀረግ የከብት አርቢ ከሆነው ስመጥር የአፋር ክልል ተወላጅ ከብቶች ዘር ግንድ ከሆኑትና የወተት ምንጭ እየተባሉ ከሚንቆለጳጰሱት ያርብቶ አደር ከብቶች ወገን ናት፡፡
 

አባቱ በመንደሪቷ ውስጥ አለ የሚባል የከብት በረት እየገለበጠ የመንደሪቷን ልጃገረድና ድርስ ጊደሮች ሚደፍር ሽንጣምና ቁመተ መለሎው፤ አሳዳጊው ቄስ ሞገሴ አፄ-በጉልበቱ እያሉ ሚጠሩት ኮርማ ነው፡፡ አባቱ አፄ-በጉልበቱ መንደሬው ዘሩን ፍለጋ ሰርክ ድርስ ጊደሩን እየያዘ ቄስ ሞገሴን ደጅ ሚጠናለት፤በቀን ከሶስት ያላነሱ ጊደሮችን አንገት ጠምዘው በግድ ሲያስጠቁት ደከመኝ የማያውቅ ወስዋሽ ጀግና ኮርማ ነበር፡፡አብዛኞቹ የመንደሪቷ ላምና ሰንጋዎች የዚሁ በውድም በግድም ጊደሮች ላይ ጥቃት አድራሽ የሆነው(አጥቂው) አፄ-በጉልበቱ የተሰኘው አባቱ አብራክ ክፋይ ናቸው በዚህም ካብዛኛው የመንደሪቷ ከብቶች ጋር የስጋ ዝምድና አለው ያባት ወገን እህትና ወንድሞቹ ናቸው፡፡
ቄስ ሞገሴና ሀጂ እንድሪስም ቢሆኑ ካንድ መንደር ኗሪነታቸውም ባለፈ ካንድ ሸንጎ የሚቀመጡ፣የተጣላን የሚያስታርቁ ሀገር ሚያከብራቸው ሽማግሎችና የልብ ወዳጅም ናቸው፡፡ ሀጂ እንድሪስ የግተ ለምለም ዘር የሆነችው ጊደራቸው ላቅመ ግንኙነት ደርሳ ኖሮ እብልቷ ፍም ሲመስል የታሰረችበትን ገመድ ልትበጥስ በረቱን እያመሰች ብታስቸግራቸው...እምቧ!!... እምቧ!! እያለች... በምቧቧ ከረዮዋ እረፍት ብትነሳቸው ረመዳን በወጣ በሳምንቱ ባንዱ ለት ማልደው ቄስ ሞገሴ ጋር ይዘዋት ሄደው ለቀበኛው ኮርማ አፄ-በጉልበቱ ቁርስ አስደረጓት፡፡ ይኽ ስጋም የስጋ ተራራ ለመባል የበቃው ሰንጋም ያን ዕለት ተፀነሰ፡፡
ገና በናቱ ማህፀን እያለ ያለቅጥ እድገት ያመጣው ፅንስ እናቱ በርግዝና ዘመኗ ከቦታ ወደ ቦታ እንዳትንቀሳቀስ ከልክሏት ባለቤቱንም ሆነ መንደርተኛውን ስጋት ውስጥ ጥሎ ነበር፡፡የናቱ የርጉዝ ሆዷ አወጣጠር ከመንታም በላይ እንደያዘች ያያት ሰው ሁሉ ጥርጣሬ አልነበረውም፡፡ግዜው ደርሶ ከረጅም ምጥ በኋላ ጥጃው ሲወለድ ግን መንደርተኛው እንዳሰበው መንቶች ሆነው አልተገኙም፡፡ ይልቁንም ገና በማለዳው የስጋ ሰንጋነቱ ውልውል ውስጥ የማይገባው አንዱ ጥጃ የሁለት ጥጆችን ግዝፈት የያዘ ጥጃ ሆኖ ተወለደ እንጂ፡፡የዚህን ገዛፋ ጥጃ መወለድ ዜናን፤ሀጂ እንድሪስ በወተት እንደምታራጫቸው ተስፋ የጣሉባት ዘረ ግተ ለምለም ጊደራቸው በሰላም መገላገሏን የሰማ ሀገሬ ሁላ ባገሩ ደንብ መሰረት የእንኳን ደስ አሎት ምኞቱን አጎረፈላቸው፡፡
ሀጂ እንድሪስም የወተት ጌታ ለመሆን ያበቃቸውን አላህ በደስታ ተሞልተው አመሰገኑ ላዲስ ውልድ ጥጃቸውም የስጋ ተራራ ሲሉ ስም አወጡለት፡፡ ከልጅነት እስከ ወይፈንነት ሲለጥቅም ላቅመ ሰንጋነት እስከበቃበት ዕድሜው ድረስ እንደ ስሙ የስጋ ተራራ እስኪያክል እየቀለቡ አሳደጉት፡፡የዚህ የስጋ ተራራ የሚመስል ሰንጋ ታሪክም ከሀረር እየተሳበ አዲስ አበቤውን በሞንሟና ስጋ አቅርቦታቸው ጉድ የሚያስብሉት ልኳንዳ አራጆች እነ ጭንቅሎ፣ ጊርጊሮና ቢላል ጆሮ ደረሰ፡፡
የበሬ ነጋዴው፣የደላላው፣የባለልኳንዳው ካልሽጡልን ውትወታ ሀጂ እንድሪስን መቀመጫ ነሳቸው፡፡ መጀመሪያ ሰሞን በእንቢታቸው ቢፀኑም “ድሮስ ገበሬ ከብት ሚያረባና ሚያደልብ ሁነኛ ጥቅም ሊያገኝበት እንጂ እበረት አጉረው አይን-አይኑን ቢያዩት ምን ዋጋ አለው!!...ደግሞም አላህ በስተርጅናዎ ደጅዎ ድረስ ያመጣሎትን እርዝቅ(አዱኛ) መግፋት ጡር አለው፡፡አላህ ክፉውን ያርቅልዎ እንጂ እንኳን የከብት የሰው ቋሚ እንደሌለው መቼም እኛ ለርስዎ አንነግሮትም፡፡ ይሄን የመሰለ የስጋ ዳሽን በከብት በሽታ ፍግም ያለ ለት ኋላ የሚተርፍዎ ፀፀት ነው” እያለ ጎረቤት መንደሩ ከምክር ደብልቆ ፍርሃት ቢነዛባቸው ነገሩን አጢነው ለፉክክር ከቀረቡ ተጫራች ልኳንደኞች አንዱ ከቃላቸው አይወጡም ለሚባሉት የልብ ወዳጃቸው እጅ መንሻ ሰጥቶ ላስጀነጀናቸው ለሳቸውም አይናቸውን ማያሹበት ዋጋ አቅርቦ ልባቸውን ላማለለው ለክርስቲያን አራጁ ጊርጊሮ ፤ እንዲሁም አንዱን ከስጋ ተራራው መለስ ያለውን ሌላ ሰንጋቸውን ደግሞ “ይኼን የስጋ ተራራ ለሌላ ሰው አሳልፈው ከሰጡ ወላሂ እቀየሞታለሁ” እያለ ለሞገታቸው ቢላል “አላህ ስጋውን ይባርክላችሁ!!” ብለው መርቀው ሸጡላቸው፡
 መቼም ሰንጋ በቁሙ እያለ ክርስቲያንም ይሁን እስላም ቤት ይደግ ሀይማኖት የለውም፡፡ሰንጋ በቁሙ እያለ ባርባ ቀኑ ክርስትና ተነስቶ ክርስቲያን ሰንጋ ተብሎ ባንገት ክሩ አይለይ?!... አሊያም ባሳዳጊ በባለቤቱ ሐይማኖት ህግ መሰረት ሰልሞ እስላም ሰንጋ ተብሎ መለያ ቆብ አይደፋ?!...መቼም ሰንጋ በቁሙ እያለ እስላሙ ለክርስቲያኑ ፤ክርስቲያኑ ለእስላሙ አልሸጥልህም፣አልገዛህም ላይባባሉ ነገር...
በሞቱ፤ባንገቱ የተሳለ ካራ ካሳረፉ በኋላ ወርችና ዳቢቱን...ሽንጥና ሻኛውን...ታላቅና ታናሹን ...ምላስና ሰንበሩን...ጎድንና ቅልጥሙን...ጉበትና ኩላሊቱን... በካራ ክርስትና ማንሳት፤ባራጁ ካራ ማስለም... ከገደሉ በኋላ ስጋውን ለገዛ ሃሳባችን...በቁሙ ቁልቢን ብለን የሸጥነውን፤ወላሂ ብለን የገዛነውን ሰንጋ ከጣልነው፣ከገፈፍነው፣ከበለትነው በኋላ ብንለያይበት፣የሚበላውን ከወዳቂው አካሉ ነጥለን ...ስጋውን ከቀንድ ና ቆዳው ለይቶ የሚያናጅስ ሐይማኖታዊ የቢስሚላሂና የበስመ-አብ ፅንሰ ሐሳብ፤ያንድ ሰንጋ ትርጉም በሁለት ልኳንዳ ቤቶች ካራ ልዩነት፣በአራጁ ምናባዊ መነባንብ…አራጁ ካራውን በሬው አንገት ላይ በሚሽጥበት ትርጉም የለሽ አቅጣጫ፤በሬውን ለመጣል እኛ በፈጠርነው የሀሳብ ዞን፤ወደ መካ፣ ወደ ምስራቅ አውድቀን በንሰሳው ውድቀትና አወዳደቅ ሃላል፣የተባረከ እያልን በከንቱ ሰዋዊ ሀሳባችን መዋደቅ ትርጉም የለሽ ይሆንብኛል...
የቀንድ ዋንጫውን፣ከቆዳው የተበጀውን ጫማና፣የቆዳ ልብስ ያለልዩነት እየተጠቀምን በስጋው መለያየት የፈለግንበት የክፋት ምርጫችን ሰማያዊነት፣ጀነታዊነት አልታይህ ይለኛል...የሐይማኖትና ሐይማኖተኞች አስተምህሮ ከፍቅርና አብሮነት ይልቅ ለልዩነት ያላቸውን የፀና አቋም አስረጂ ይመስለኛል፡፡ አባ ለሚካዔል ያመት ንግስ ለት ለቅዳሴ ከቤትዋ ሲወጡ ያረጉት መጫሚያዎ ሲረግጡት ቢስሚላሂ!!...ቢስሚላሂ!!...ያ-አላህ!!..ያ-አላህ!! ይላል…ምነው የእስላምና ክርስቲያን ስጋ ሲለዩ …የእስላምና ክርስቲያን ቆዳ መለየት ተሳንዎ?!... ሀጂ ለጁምዓ ለት ስግደት ሲሄዱ ያረጉት መጫሚያዎ ሲረግጡት በስማብ-በወልድ!!...በስማብ-በወልድ!!...ምነው በድንግሊቷ?!...ምነው በኡራኤል!!...ይላል እርስዎስ ቢሆኑ ምነው የእስላምና ክርስቲያን ስጋ ሲለዩ …የእስላምና ክርስቲያን  ቆዳ መለየት ተሳንዎ?!...


ይህቺን ሊንክ ከልከው https://www.facebook.com/kindeta ዘለቅ ብለው ያንብቡኝ!!... እርሶም የመውደጃ ምልክተዋን ተጭነው መውደድ- መዋደድዎን አይርሱ?! ለወዳጅዎም ግብዣ ይላኩ፡፡

0 comments