Showing posts with label Culture. Show all posts
Showing posts with label Culture. Show all posts

Wednesday, August 19, 2015

የኔ አባት ገበሬው (ሄኖክ የሺጥላ)

የኔ አባት ገበሬው ( ሄኖክ የሺጥላ )
የኔ አባት እሱ ነው አባይ ስር የነቃ
ሃገሩን ያነቃ
አንቅቶ ያለፈ
አልፎ የገዘፈ ።

የኔ አባት ገበሬው
ቃላት እና ዘየው
ዘየና ዝማሬው
ዝማሬና ስራው
የሲና ላይ በትር
ጦሩን ሲነቀንቅ
ቀስቱን ሲያነጣጥር
አነጣጥሮ ሲጥል
የጣለው ሲያጣጥር
እዩት ሲንጎማለል
ዝናር በወገቡ
ጋሻና ጥሩሩ
ኢትዮጵያ ናት ክብሩ !
የኔ አባት ገበሬው
አፈሩን ሲገፋ
ሲገፋ ሲለፋ
ዋሽንቱን ሲነፋ
ነዶውን ሲቀምር
በሮቹን ሲጠምር
ሲወቃ ሲያ-በራይ
አገዳን ከግቻ
ሲነጥል ሲለያይ ።
የኔ አባት ገበሬው
አልቤኑ ነው አልቦው
ሰኔ-ጎሎጎታው ፣ ማረሻና ወገሉ
ግማሽ ጎን አካሉ
ፍቅር ነው እምነቱ
እምነቱ ነው-ቃሉ !
የኔ አባት ገበሬው
አሂዶ ያስሄደ
ጤፍን ያስዘመመ
አደይ ያነጠፈ
ለሀገር እዮሃ ዘርዶ የዘነጠፈ
ግልገል እና ደቦል አጣምሮ ያቀፈ ።
የኔ አባት ገበሬው
እምነቱ ነው ሃብቱ
ፍቅሩ ነው ንብረቱ
ተዋዶ መኖሩ
ተካፍሎ መብላቱ !
የኔ አባት ገበሬው
የኦፊር ስጦታ
የራማ ነጭ እጣን
ሚኒሊክ ሚኒሊክ ፣ የሶሎሞን እጣን
የሰብ’አ ጥር
ውልደትን አብሳሪ
ተጏዥ በጨረቃ
በኮከብ ምልክት ፣ በአምላክ ፍቅር ሲቃ
የኩሽ ምድር ንጉስ የግብጦች አለቃ !
የኔ አባት ገበሬው ነጻነት አይነቱ
የደሙ ቀለም ነው እምቢ ወንድነቱ !
ሞትን የደፈረ
በመድፈር የኖረ
በሕይወት ምልአት
በዜማ ቅኔ ቤት
የተገመደ እውነት ።
ላገሩ ነጻነት
ጥይት ለነብሱ ሕይወት
አ! ብሎ የጠጣ
ጠጥቶ ያለፈ
አልፎ የገዘፈ !
እምቢ ዝባዝንኬ
ዝባዝንኬ ዘኬ
ላገሬ ነጻነት
አባቴ ነው ልኬ
አባቴ ነው መልኬ
እንቢ ! እንቢ ! እንቢ ! እንቢ ! እንቢ !

Sunday, August 16, 2015

"ግጥም እንደ አልጌ ሲፋቅ ጭረት አለው"

ሀያሲ አብደላ እዝራ:-
ዛሬ ቅዳሜ ነው! በዚህች ቀን በርካታ አስደሳች የህይወት አጋጣሚዎች አልፈዋል:: ካለፉት ጊዜያቶች ሁሉ ደግሞ የዛሬ ልዩ ነው፡፡ ለብዙ ዓመታት ደንበኛ በሆንኳትና በምወዳት አዲስ አድማስ ጋዜጣ ላይ በስነፅሁፍ ህይወቴ ለራሴ ክብር የሰጠሁበትና ወደፊት ጠንክሬ እንድፅፍ ምርኩዝ የሆነኝ አስተያየት በአካልም ሆነ በመልክ የማላውቀው ሀገራችን በኪነጥበብ ዘርፍ ካፈራቻቸውና በስነ ፅሁፍና ግጥም ዙርያ ጠንካራ ሂስ በመስጠት የሚታወቁት ሀያሲ አብደላ እዝራ እጅ የግጥም መፅሀፌ ገብታ ከፍተኛ ትኩረት አግኝታ ተገምግማ ለወደፊት ስራዬ የሚያስፈነጥረኝን እርካብ እንደመርገጥ ምን የሚያስደስት ነገር አለ?!::
እኚሁ ሀያሲ ማክሰኞ ነሀሴ 12/2007 ዓም በፑሽኪን አዳራሽ ከምሽቱ 11 ጀምሮ በተሰናዳው የመፅሀፍየምረቃ ዝግጅት ላይም እንደዚህ ቀልባቸውን ስለሳበችው መፅሀፍ ከዚህ ለየት ያለ ሙያዊ አስተያየት ሊያቀርቡ ፕሮግራም ተይዞላቸዋል፡፡ እኔም እኚህን ሰው እኩል ከናንተ ጋር ለማየት ጓጉቻለሁ፡፡
የዛ ሰው ይበለን
መልካም ቅዳሜ