Wednesday, August 19, 2015

የኔ አባት ገበሬው (ሄኖክ የሺጥላ)

የኔ አባት ገበሬው ( ሄኖክ የሺጥላ )
የኔ አባት እሱ ነው አባይ ስር የነቃ
ሃገሩን ያነቃ
አንቅቶ ያለፈ
አልፎ የገዘፈ ።

የኔ አባት ገበሬው
ቃላት እና ዘየው
ዘየና ዝማሬው
ዝማሬና ስራው
የሲና ላይ በትር
ጦሩን ሲነቀንቅ
ቀስቱን ሲያነጣጥር
አነጣጥሮ ሲጥል
የጣለው ሲያጣጥር
እዩት ሲንጎማለል
ዝናር በወገቡ
ጋሻና ጥሩሩ
ኢትዮጵያ ናት ክብሩ !
የኔ አባት ገበሬው
አፈሩን ሲገፋ
ሲገፋ ሲለፋ
ዋሽንቱን ሲነፋ
ነዶውን ሲቀምር
በሮቹን ሲጠምር
ሲወቃ ሲያ-በራይ
አገዳን ከግቻ
ሲነጥል ሲለያይ ።
የኔ አባት ገበሬው
አልቤኑ ነው አልቦው
ሰኔ-ጎሎጎታው ፣ ማረሻና ወገሉ
ግማሽ ጎን አካሉ
ፍቅር ነው እምነቱ
እምነቱ ነው-ቃሉ !
የኔ አባት ገበሬው
አሂዶ ያስሄደ
ጤፍን ያስዘመመ
አደይ ያነጠፈ
ለሀገር እዮሃ ዘርዶ የዘነጠፈ
ግልገል እና ደቦል አጣምሮ ያቀፈ ።
የኔ አባት ገበሬው
እምነቱ ነው ሃብቱ
ፍቅሩ ነው ንብረቱ
ተዋዶ መኖሩ
ተካፍሎ መብላቱ !
የኔ አባት ገበሬው
የኦፊር ስጦታ
የራማ ነጭ እጣን
ሚኒሊክ ሚኒሊክ ፣ የሶሎሞን እጣን
የሰብ’አ ጥር
ውልደትን አብሳሪ
ተጏዥ በጨረቃ
በኮከብ ምልክት ፣ በአምላክ ፍቅር ሲቃ
የኩሽ ምድር ንጉስ የግብጦች አለቃ !
የኔ አባት ገበሬው ነጻነት አይነቱ
የደሙ ቀለም ነው እምቢ ወንድነቱ !
ሞትን የደፈረ
በመድፈር የኖረ
በሕይወት ምልአት
በዜማ ቅኔ ቤት
የተገመደ እውነት ።
ላገሩ ነጻነት
ጥይት ለነብሱ ሕይወት
አ! ብሎ የጠጣ
ጠጥቶ ያለፈ
አልፎ የገዘፈ !
እምቢ ዝባዝንኬ
ዝባዝንኬ ዘኬ
ላገሬ ነጻነት
አባቴ ነው ልኬ
አባቴ ነው መልኬ
እንቢ ! እንቢ ! እንቢ ! እንቢ ! እንቢ !

0 comments