የተገነባንበትን ማህበረሰባዊ ስርዐት መለስ ብለን መፈተሽና የተጣመመው የማቃናት፣የተበላሸውን የማረም ስንዴውን ከገለባው፤አበቁን ከፍሬው አንፍሶ አበጥሮ የመለየት ስር ነቀል ማህበረሰባዊ ለውጥ እንዲመጣ
እንደ ውሀ ላይ ኩበት የሚዋልለውን ኢትዮጵያዊ ማንነት በእውቀት እና በጥበብ ብርሃን እንዲመራ፣ በደመነፍስ ሳይሆን በአመክንዮና
በሃሳብ ፍጭት የጠራ፣ በስሜት ሳይሆን በምክንያት የሚያምን ትውልድ የመፍጠር
ስራ የማን ድርሻ ነው?!
የወቅቱ ፖለቲካ አራማጆች እንደሚሉት ለሀገር እድገትና ቀጣይነት የሚያስፈለገው(ልማታዊ
አመለካከት) የቴክኖሎጂ እና መሰረተልማት ማስፋፋትን ያስቀደመ የአብዮታዊ ዲሞክራሲ ፖለቲካዊ አቀንቅኖ በመንገድና ሌሎች መሰል ያረጁ
ህንፃዎችን አፍርሶ ለመገንባት የሌሎችን እውቀትና ስልጣኔን ምርኩዝ ማድረግ፤ ወይንም ድሮ-ድሮ በስልጣኔ እንመራው የነበረው ዛሬ
ግን ጭራውን እንኳን ለመያዝ የተሳነን የምዕራባውያን ስልጣኔ... በአስደናቂ ኢኮኖሚያዊ እድገታቸው ለሌሎች በምሳሌነት የሚጠቀሱ
የኤዥያ ሀገራት ዜጎችን እውቀትና ልምድ ላይ የተንጠለጠለ፤ የቴክኖሎጂ
ሽግግር በሚሉት ፖለቲካዊ ድስኩርና ለፖለቲካዊ ፍጆታ የሚውል ጊዜያዊ ችግርን ከመቅረፍ በቀር...እንደኔ እምነት አርቆ ለሚያስብ
ሀገር እና ህዝብ የፍልስፍና መሰረት አሊያም ሃገር የሚመራበት ቀመር
ሊሆን የማይበቃ፣ ውሀ የማያነሳ ሀሳብን ተቀብሎ እንደፈለጉ ያድርጉትን በመፍትሄነት ወስዶ ጆሮ ዳባ ልበስ የሚል ማህበረሰብ እየፈጠረ
የነበረና ያለን ስርዐት ተቀብሎ በድንዛዜ ውስጥ የሚኖር ኢትዮጵያዊነት ከየት መጣ?!
እኛ ኢትዮጵያውያን በቀደምት ንጉሳዊና የፊውዳል ስርዐቶች እርስ-በእርስ በሚደረግ የስልጣንና የዘር ሃረግ ቆጠራ በወለዳቸው
ሽኩቻዎች የባከኑብንን ጊዜያት፣የስልጣኔ ጀማሪዎች ነን ብለን የምንመፃደቀበት ታሪካችን ጋር የሚጣረስ በአፈ-ታሪክ እንጂ...ከትውልድ
ትውልድ ሲሸጋገር ያላየነው በጥቂት ድርሳናት፣ታሪካዊ ቅርሶችና የኪነ-ህንፃ ጥበብ ውጤቶች ላይ ብቻ የምናየው ያለፈው ዘመን አሻራ
ከኛ ለቀደመውም ሆነ አሁን ላለነው ትውልዶች ግንጥል ጌጥ የሆነ ስልጣኔያችን...የታሪክ እንጂ የእውቀትና የጥበብ መሰረት የሌለው
የስልጣኔ ታሪካችን...ለዛሬ ማንነታችን፣ኢትዮጵያዊነት ቀለማችን ከጆሮ ጌጥነት ያልዘለለ ፋይዳ የሌለው ከአንድ ጥርብ ድንጋይ አያቶቻችን
ፈልፍለው እንደሰሩት የቁም ድንጋይ (ስነ-ቅርፅ አክሱማችን) አሁንም በኛ ዘመን ቆሞና ወድቆ ስናየው የኛ በመሆኑ ባለፈ እና እንደ
አክሱም አንድ ዘመን ላይ ተገትሮ በቀረው የቅድመ አያቶቻችንና ምንጅላቶቻችን ፈር ቀዳጅ ስልጣኔ እና በዛሬይቱ ኢትዪጵያና ኢትዪጵያውያን
ጥበብ፣እውቀትና ስልጣኔ መካከል ያለውን የተበጠሰ፤ ለዘመናት በአፋዊ ቅብብሎሽ እየደበዘዘ፣ ከእውነታነት ወደ ልብወለድነት፣ከእውቀትነት
ወደ ተረትነት እየተቀየረ የመጣውን ያለፈውን ኢትዮጵያዊ ማንነት ከዛሬው ማንነታችን ጋር ያለውን ትልቅ ክፍተት የምንሞላበት የማንነታችንን፣የታሪክና
ባህላችንን ስሩን ይዘን፣የቱባውን ውል መዘን ያለፍት መቶ አመታት ታሪካችን ጋር የምንቋጥርበት ብልሀቱ ጠፍቶን፣ጥቂት አዋቂዎቻችን
የሞከሩት ግን ደግሞ በግለሰብ ላይ ብቻ የተንጠለጠለ፣ሀገራዊ መሰረት የሌለው የእውቀትና የጥበብ ትውልዳዊ ሽግግር...የዛሬው ኢትዮጵያዊ
ማንነታችን በፀና መሰረት ላይ እንዳይቆም ያደረገውን... በራስ ወዳዶች የተገነባ የፖለቲካና የማህበረሰብ ስርአትን በዕውቀትና በጥበብ
የማንፈትሸው ለምንድነው?!
ያለፉት ዘመናት ሀይማኖታዊ መሰረት የያዘ የፖለቲካ፣የባህልና የእምነት ማህበረሰባዊ ስርአታችን የዛሬው ኢትዮጵያዊ ማንነታችን ላይ የፈጠረውን ድንዛዜ... የአሁኑም
ሆነ ያለፈው ንጉሳዊ ስርዐት ለመሪዎቹና ለስርዐቱ አጫፋሪዎች፣በአምቻና ጋብቻ፣በዘርና በጎሳ ልዩነት የጥቂቶችን ኑሮ የተደላደለ ያደረገ
ብዙዎች በእውቀትና በኢኮኖሚ ድህነት ሲንፏቀቁ ጥቂቶች ሀይማኖታዊ፣ፖለቲካዊ ዶግማዎችንና እውቀታቸውን ለፖለቲካ መሳሪያነት ተጠቅመው
ለብዙሃን ሳይሆን ለጥቂቶች ፤የሚያገለግል ውስን ቀድመው የነቁ የማህበረሰብ ክፍሎችን ተጠቃሚ ያደርግ የነበረ ፖለቲካዊና ማህበረሰባዊ
ስርአት ፣ በሀይማኖትና በባህል ዶግማ የተተበተበ የማህበረሰብ ስርአት... ዛሬም መልኩን ቀይሮ ከብዙሃን ይልቅ ጥቂቶች የሚንቧቹበት
ፖለቲካዊ ስርአት ተጭኖን ፣ትክሻችን ጎብጦ ...ለምን ብለን ከመጠየቅ በዘልማድና በደመነፍስ የመኖር አባዜ ብዙ ሺህ አመታት ተሻግሮ
ዛሬም ድረስ ግለሰባዊ እምነት፣እውነትና ፍልስፍናችንን ማንቁርቱን ይዞ ዛሬም በልማድና በመንጋ የመኖርን ብሂልን ትክክል ነው ብለን
ተቀብለን እንድንኖር ያደረገንን... በዝምታ ፣በቸልተኝነትና በምናገባኝ አዚም ተውጠን፣ደንዝዘን ምክንያት አልባ ህይወት የምንኖር
ህዘቦች መሆናችን ዛሬም ጥያቄ የማይፈጥርብን ለምን እንደሆነ ሳስብ በራሴ አፍራለሁ፡፡
ዘመናዊ ትምህርት መስፋፋት ከጀመረበት ጊዜ አንስቶ የተመሰረቱ አንጋፋ ዩኒቨርስቲዎች የወርቅና የብር እዩቤልዩ በአላቸውን
ከማክበር ውጭ የፈጠሩት ኢትዮጵያዊ እውቀት መሰረት የት ጋር ነው ያለው ?! ይኼን ማንሳቴ ጥቂት ግለሰቦች በኢትዮጵያዊነት ስሜት ተቃጥለው፣በኢትዮጵያዊነት ስሜት ነደው የሰሯቸው ውስን የታሪክ፣የኪነጥበብ፣የፍልስፍናና የማህበረሰብ ሳይንስ
ፈጠራና እውቀትን መሰረት አድርጎ እነዚህ ስለትውልድና ሀገር የሚገዳቸው ጥቂቶች የጀመሩትን ኢትዮጵያዊ ማንነት በኢትዮጵያዊ እውቀትና
ጥበብ የማነፅ በጎ ተግባርን መሰረት እንዲይዝ እያሳደገ ፣እያዳበረ፣የራሱን እየጨመረ ለመጪው ትውልድ የማስተላለፍ እሴት ፣ዛሬን
ሳይሆን ነገን አርቆ የሚያስብ ስለሃገሩና ወገኑ የሚገደው ኢትዮጵያዊ ብልጭ ድርግም ሲል..እውቀትና ጥበብ ከግለሰቦቹ ጋር አብሮ
ሲቀበር፣ለግለሰቦቹ የቀብር ስርዐት ማስፈፀሚያ፤ የህይወት ታሪክ ማድመቂያ ሆኖ ሲቀር ...ይኽ ማህበረሰባዊ ስርዐት እንደ ድመት
የወለዳቸውን መልሶ እየበላ፣ሳያብቡ እየቀጠፈ፣ሳያፈሩ እያረገፈ እያየን ዛሬም ቁብ የማይሰጠን ህዝቦች መሆናችን እኔን ያስጨንቀኛል፤እንደኔ
እቤታቸው ቁጭ ብለው እጅና እግራቸውን አጣጥፈው የሚጨነቁ፤ኢትዮጵያዊነታችን ወዴት እየሄደ ነው ብለው በእልህ የሚናጡ ቀና ኢትዮጵያውያን
መኖራቸውን አልጠራጠርም፡፡
አንገብጋቢውና ትልቁ ነገር ጓዳ ውስጥ ቁጭ ብሎ መቆጨትና መንገብገቡ አይደለም ፡፡ካለፉት ስርዐቶች ጀምሮ መልክና
ቅርፁን እየቀየረ ዛሬ ድረስ እንደ ምርግ ተጭኖን ፣ እንደ አህያ እንደፈለጉት ሲጭኑን አንዳንዴ ክብደቱ ሲበዛብን፣ምሬት ሲንጠን
በልምጭና በሀይል ጥቂቶች ባበጁልን ጎዳና መጓዝን ተላምደነው የምንኖረው ሀይማኖታዊና ባህላዊ መሰረት ያለው በእውቀትና በጥበብ ያልተቃኘ ፣በፍልስፍና ያልተወቀሰ፣ያልተከሰሰ
ማህበረሰባዊ ስርዐታችን ዛሬም ለጥቂቶች፣ለሀገር ሳይሆን ለግለሰብ መጠቀሚያነት የሚያገለግል ፖለቲካዊ ስርአትን፣የሀይማኖት ተቋማትን
ዶግማና አስተምህሮ በሀይልና በጉለበት ሳይሆን በእውቀትና በጥበብ የመታገል፣ለምን ብሎ የመጠየቅ፣ራስ ነቅቶ ሌሎቹን የማንቃት፣በነፃነት
የሚያስብ ፣በምክንያትና ውጤት የሚያምን፣የሌሎችን ሀሳብ በጭፍን የሚጠላ፣በጭፍን የሚፈርጅ ሳይሆን መርምሮና መዝኖ የሚቀበል፤ በጎውን
ከክፉው ለይቶ እንጂ በጅምላ ከማሰብና ከቡድንተኝነት ስሜት የተላቀቀ ከሀይማኖታዊ፣ባህላዊ አንድ ዘመም የፖለቲካዊ አመለካከት እስራቶች
ነፃ የሆነ ሀገርና ህዝብ ለመፍጠር ግለሰባዊ ድርሻን መወጣት ያስፈልጋል፡፡
እነዚህን ለዘመናት በድንዛዜ ውስጥ ያኖረንን፣በነፃነት የማሰብ፣የመመራመር፣የመፈላሰፍ፣ለምን ብሎ የመጠየቅ፣በአደባባይ
የግል እምነትና አመለካከታችንን ለመግለፅ እንዳንችል ልምሻ ያደረገንን፣አይምሮአችንን ጨምድዶ፣ተብትቦ የያዘንን ስርዐት፤ ለምናምነው
ነገር በፅናት እንዳንቆም በፍርሀትና በይሉኝታ ሸብቦና -ቀፍድዶ፤በፍርሀት ጨለማ ውስጥ በእውር-ድንብር የሚያኳትነንን...እኛ የምናምነውን
ካላመንክ ፣እኛ የምናስበውን ካላሰብክ፣እኛ እናውቅልሀለን የሚሉ...የኛ ተነፋነፍ ሱሪ ነው ልክህ፣የኛን ነጠላ ካላገለደምክ የሚሉ፣የሃሳብ
ነፃነት ድንበር የሚያበጁ...እንደ ስብሐት ገ/እግዚያብሄር አይነት የሀሳብ ነፃነትን፣የማህበረሰብ እስራትን አንቀበልም ብለው የሚያፈነግጡ...የሚያምኑበትን
መፃፍ ብቻ ሳይሆን የሚኖሩ ፈላስፋዎችን የስድነት ታርጋ በመለጠፍ፣የነውረኝነት ካባ በማልበስ፣ፍልስፍናቸውን እና ሀሳባቸውን በጥልቀት
ከመመርመር ይልቅ፣በማነወርና በማጥላላት ሌሎች እንዳያውቁ፣እንዳይነቁ ባህልና ወጋችን አይፈቅድም በሚል የሃሳብ ሸምቀቆ ሸምቅቀውና
አስረው በጅምላ እንድናስብ፣በስሜት እንድንነዳ የሚፈልጉ ሀይማኖተኞችና ፖለቲከኞች በሚቀዱት ቦይ ብቻ እንድንፈስ ለራሳቸውና ለተከታዮቻቸው
ጥቅም ካልሆነ በቀር ለሀገርና ህዝብ እርባና የሌለው እንቶፈንቶአቸውን እንደእናቶቻችን አፍንጫችንን ሰንገው ሲግቱን አሜን ብለን
በደመ ነፍስ እንድንኖር ...የአስመሳይነት በግ ለምድ ለብሰው ለራስ ካልሆነ በቀር ለሌሎች ማሰብ፣ለሀገርና ለህዝብ መቆርቆር እንደ
ሞኝነት፣እንደ አላዋቂነት የሚቆጥር የማህበረሰብ ስርዐት...
በተወሰኑ የባህል፣የሃይማኖት እና የፖለቲካ አመለካከት አጥሮች ታጥረን እንደአንበሳ ግቢ አንበሶች ማንነታችን ጠፍቶ...አንበሳዊ
መልካችን እንጂ አንበሳዊ ነፃነታችን ተገፎ፣የምናምነውን ፣የምናስበውን እንዳንሆን አይደፈሬውን አጥር እየፈራን እንድንኖር...የተበጀልንን
የአይምሮ ካቴና ግለሰባዊ እውቀትና ጥበብን፣ነፃ አመለካከትንና አስተሳሰብን የሚያመክን የጅምላና መንጋዊ አስተሳሰብ ፣በእውቀትና
በጥበብ ሳይሆን በስሜት እንድንገነፍል፣የቡድንና የግለሰብ አጀንዳ ማስፈፀሚያ ፣በብዙሃን ደም ላይ ተረማምደው ስልጣንና ሀይልን ለመቆናጠጥ
የሚፈልጉ ብልጣብልጦች መጠቀሚያ እንድንሆን፣እነሱ ያወቁትን እንዳናውቅ፣ሌሎችን የመምሰል፣ሌሎችን የመቅዳት፣እንደራስ ሳይሆን እንደሌሎች
መኖርን፣ወደ ራስ ከመመልከት ይልቅ ወደ ሌሎች መጠቆምን፤ለራስ ድክመትና ውድቀት ሌሎችን ተጠያቂ የሚያደርግ...ሌሎችን መኮነን እና
ማብጠልጠል እንደ መፍትሄ የሚቆጥር ትውልድና ህዝብ እያፈራ ያለን ማህበረሰባዊ ስርዐት...
አንድ ጊዜ ካለመናገር ደጃዝማችነት ይቀራል፤ሌላ ጊዜ ዝም አይነቅዝም፣ዝምታ ወርቅ ነው፣ዝም ባለ አፍ ዝንብ አይገባበትም
በሚል እርስ በርሱ በሚጣረስ ተረትና ምሳሌ ግለሰባዊ የሃሳብ ነፃነትን መገደቢያ ብሂሎችን በመደንቀር በራሱ የማይተማመን፣ለሚያምንበት
ነገር በቁርጠኝነት ላለመቆም ሰንካላ ምክንያቶች እንደ በገና የሚደረድር ሀገር ተረካቢ ዜጋ...ሀገሩን ጥሎ ለመሄድ ሞት እንኳ የማያቆመው
ኢትዮጵያዊ ወገን...አያቶቹ ዝናብ ፍለጋ ወደ ሰማይ ያንጋጥጡ እንደነበረው...ወደ ሰው ሀገር ሚያንጋጥጥ ስደተኛ ወጣት እየፈጠረ
ያለን ማህበረሰባዊ ስርዐት...
ማህበረሰባዊ እስራቱን ጥሰው፣ወግ ልማዱን ዘለው፣ገደብና
አጥሩን ፈግጠው ከመንጋው መሀል ነጥረው የሚወጡ ጥቂቶች ቢፈጠሩ እንኳን እየጎተተ ወደ ኋላ የሚያስቀር፣እየጠለፈ የሚጥል ማህበረሰባዊ
ስርዐታችንን ዛሬም የማንጠይቅበት ምክንያት ምን ሊባል ይችላል...ኢትዮጵያዊ እውቀት ጨርሶውኑ ደብዛው ሲጠፋ አይተን እንዳላየን
-ሰምተን እንዳልሰማን የምናልፍበት ዘመን አብቅቶ ራሳችንን ዞር ብለን መመርመር፣መፈተሽ የሚያስፈልግበት ወቅት ላይ የደረስን ይመስለኛል፡፡
0 comments