Sunday, October 4, 2015

ጦማር ፫



ቀን፡- መስከረም 23፣ 2007ዓ.ም
ጦማር ፫

ቢደርስም፤ባይደርስም ለተከበሩ ጠቅላይ ሚኒስትር አቶ ኃይለማርያም ደሳለኝ


ከ፡-ሱራፌል ሐቢብ

 
      የጦማር ወግ አጀማመር ደህንነትን መጠየቅ ቢሆንም የእርስዎን ደህንነት መጠየቅ ሌሎች ደህንነታቸው ሊጠየቅ የሚገባ ሰዎች ላይ አንደማሾፍ ሰለሚቆጠርብኝና በእርስዎ ደህንነትም ላይ ስጋት ስለሌለኝ ደህንነትዎን በመጠየቅ ዝባዝነኬ አላበዛብዎትም፤ አርስዎ ምን ይሆናሉ? አኛ ነን አንጂ በኑሮ ውድነት፣በፍትህ እጦት፣ በሰብአዊ መብት ጥሰት እና በአሳብ መከልከል የምንገላታ!!
      ከዚህ በፊት በላኩልዎ ሁለት ጦማሮች ባለፈው ምርጫ ፓርቲዎ በከፍተኛ ችከላ 100% በማግኘት ፓርላማውን የማህበራችሁ የግል ርስት ማድረጉ አጅግ አስነዋሪ ስራ (እንደውም ሴራ ቢባል የተሻለ ነው) መሆኑንና ተቀባይነት የሌለው ድርጊት አንደሆነ አበክሬ ገልጬልዎታለው፡፡ ክቡርነትዎ፡- እናም በዚህ የማህበራችሁ ነፃ ርስት ላይ አንድ ዓይነት የአሳብ ዘር ለመዝራት እርሻውን  በነገው እለት ማለትም መስከረም 24/2008 ዓ.ም  በይፋ አስቀድሞ  ሁለቱን  በሬዎች(አፈጉባዬዎቹን)  በመጥመድ አስከትሎም ለይስሙላም ቢሆን አርስዎን አንደዋነኛ አራሽ አድርጎ ለመሾም የሰዓታት አድሜ ነው የቀረው፡፡ ክቡር ጠቅላይ ሚኒስትር፡-  አስከዛሬ ድረስ ፓርቲያችሁ መንግሰት ከሆነበት ጊዜ አንስቶ ሊቀመንበሩን መራሔ መንግሰት አደርጎ የመሾም ታሪኩ ተቀይሮ ስለማያውቅ አርስዎም የቀጣይ ዘመናት መራሔ መንግሰትነትዎ ለርግጠኝነት በተጠጋ ግምት  ረግቶ የሚቆይ መስሎ ስለተሰማኝ ነው  “ዋነኛ አራሽ” ይሆናሉ ብዬ ማለቴ ፡፡

      ክቡርነትዎ፡- መቼም ካልናቁኝ አንድ ምክር ልምከርዎ፤ ባለፈው ጠቅላላ ጉባዬችሁ ማብቂያ ላይ ለቀጣይ ጉባኤ ከሁለት ዓመት በኋላ አዋሳ ላይ እንገናኝ ተባብላችሁ ነው አሉ የተለያያችሁት፤ ይህ ትልቅ ስህተት አንደሆነ ግን ዳግም መገምገም ይኖርባችዋል! ለምን ቢሉ? ለብቻችሁ በያዘችሁት ርስት በፓርላማው ላይ ማከናወን የምትችሉትን ትንሽ ጉዳይ  ለምን በመንከራትት  ታገዝፉታላችሁ?! አርስዎም ቢሆኑ የመንግሰትዎ ስራ ብዙ ነው፣ ስራ ይበዛብዎታል፤ አንደው  አግረ መንገድዎን  ዘመዶችዎን  ለመጠየቅ ካላሰቡ በቀር አዋሳ ድረስ ሔደው ለምን ጊዜዎን ያባክናሉ  እዛው ከቢሮዎ በሁለት አርምጃ በማይርቀው ርስት ፓርላማችሁ ውስጥ መሰብሰቡ አይሻልም ይላሉ? አመኑኝ ለእርስዎም ሆነ ለስብስባችሁ የተሻለ አማራጭ ነው! ማን አለባችሁ? በሙላ አናንተው ናችሁ!!! ምን የሚያሰጋ ነገር አለ ብለው ነው?  ሕዝቡ ምን ይለናል ብላችሁ ከሆነ፤ ሕዝቡ ምንም አይልም! አራሱ አይደል እንዴ 100% የመረጣችሁ? ደግሞም በኑሮው ስንት አሳብ አለበት መሰልዎ፤ ስብሰባችሁ የፓርላማ መደበኛ ጉባኤ ይሁን ወላ  የፓርቲያችሁ ጠቅላላ ጉባኤ ግድም አይሰጠው፤ እናም “ይድላሽ ተንቧቺበት”  አንዳለው ዘፋኝ የአሻችሁን ታረጉ ዘንድ ሕዝቡ የፈቀደ ይመስለኛል፤ ስለዚህ ይህ ምክሬን ጣል አርገው ባያልፉ የሚሻል ይመስለኛል፤ የግድ እርስዎን ለማማከር የአብዮታዊ ዲሞክራሲ ካባ ለብሼ፣ ኅሊናዬን ሽጬና ከርሴን አስፍቼ በሚኒስትር ማዕረግ የጠቅላይ ሚኒሰትሩ አማካሪ ተብዬ መሾም አለብኝ?!       
      ክቡርነትዎ፡- የርስታችሁ መናብረት በማህበራችሁ አባላት የተሞላ ቢሆንም፤ የስርአቱን አፋኝነት፣ የፖሊሲ ጥመት እና ቀሽም ሀገር የማስተዳደር ብቃት ባላቸው የእውቀት መጠን የሚተቹና፣ በሰላና በበሰለ ብዕራቸው ቁልጭ አርገው ለሕዝቡ የሚያሳዩ ብዙ የፖለቲካ ፀሐፍት በአካል ከርስታችሁ ወንበር ላይ ባይቀመጡም  በየቦታው ባለ መቀመጫቸው እንዳሉ ግን አይዘንጉ፤ ዳሩ! ክቡርነትዎ ቢዘነጉም ሆነ ቢያስተውሉ ምን ዋጋ አለው?! ደህንነትዎችዎ የፀሐፊያኑን እጅ ብዕር አስጥለው በካቴና ይጠፈንጉልዎታል፤  ምን ተዳዎ አርስዎማ!!! ግና የያገባኛል መንፈስ ፍሬ እያፈራ ለመሆኑ አመሰክርልዎታለው!!!
ክቡር ጠቅላይ ሚኒሰትር፡- በመጨረሻም  ዳግም  መራሔ መንግሰት  ሆነው የመሾም እድልዎ ከበፊት የድርጅትዎ ታሪክ መነሻነት አይቀሬ ነው ብዬ አንደምገምት ከላይ ገልፄልዎታለሁ፤ እናም ሹመት ያዳብር አንዳልልዎ ከዚህ በላይ የዳበረ እና የደለበ ሹመት የለምና ተገቢ አይመስለኝም፤ በዛ ላይ የጦር ኃይሎች ጠቅላይ አዛዥ መሆንዎም ድራቢ መሆኑን አይርሱ፤ እነእንትና አርስዎን ከፊት አቁመው ከጀርባ ስራቸውን ይሰራሉ፤ ሴራቸውንም ያሴራሉ ፤ ሆነም ቀረ እኔም ካለሁበት 548 መቀመጫዬ ላይ ሆኜ በሀገሬ ጉዳይ ላይ  ልትውስኑ የሚገባውን ሁሉ አየተከታተልኩ ውጤት አልባ ድምፄን አጮሀለሁ!  አስከዚያው ለራሴ ስላምንና ጤናን አየተመኘሁ!! ዳግም ሰፋ ባለ ጉዳይ አሰክፅፍልዎ ደህና ልሁን!!!! 
       

0 comments