Wednesday, August 19, 2015

በኢህአዴግ አድናቂ ማብዛት ያስገመግማል!

ሚኒስትሩ ዳያስፖራውን ሲያዝናኑና ሲፈርሙ አመሹ

    የቀድሞው ጠ/ሚኒስትር መለስ ዜናዊ (መሬት ይቅለላቸውና!) ፓርቲያቸው ኢህአዴግ ሥልጣን በያዘ ማግስት፣ ከአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ ምሁራን ጋር ለውይይት መቀመጣቸው ይታወሳል፡፡ (ውይይት ሳይሆን ሽንቆጣ ነው የሚሉም አሉ!) 

በእርግጥ ማንም ቢሆን ጠ/ሚኒስትሩ ከምሁራኑ ጋር ይወዳደሳሉ ብሎ ሊገምት አይችልም (የመተኳኮስ እንጂ የመወዳደስ ታሪክ የለንም!) ለነገሩ ምሁራኑም ቢሆኑ ጠ/ሚኒስትሩን በዝምታ አላለፏቸውም፡፡ የቻሉትን ያህል በነገር ወጋ ወጋ አድርገዋቸል ይባላል፡፡ (40ዎቹ የዩኒቨርሲቲ መምህራን የተባረሩት ከውይይቱ በፊት ነው በኋላ?) 
የሆነ ሆኖ ውይይቱ በሉት ሽንቆጣው ከተጠናቀቀ በኋላ ጠ/ሚኒስትሩ የተማሪነት ዘመን ዶርማቸውን የጐበኙ መሰለኝ (ሩብ ክ/ዘመን ስለሞላው ብሳሳት ወይም ብስት አትፍረዱብኝ!) እናላችሁ … ያን ጊዜ ነው ምድረ ምሁር በሰልፍ ጠ/ሚኒስትሩን ሲያስፈርም በኢቲቪ መስኮት የተመለከትነው፡፡ (የታዘብነው ለማለት ፈልጌ ነው!) ከፍተኛ የመንግስት ባለሥልጣን … ያውም አድራጊ ፈጣሪ የአገሪቱ መሪ … ድግሪ ለጫኑ አድናቂዎቹ ሲፈርም ለመጀመሪያ ጊዜ ያየሁትና የተገረምኩት ያኔ ነው፡፡ 
ለነገሩ ሁኔታው ለጠ/ሚኒስትሩም ዱብዕዳ ሊሆንባቸው እንደሚችል አያጠራጥርም፡፡ (ድንገተኛ መስሎኝ?!) አልነገሩንም እንጂ ጠ/ሚኒስትሩ በፓርቲያቸው ክፉኛ ተገምግመውም ይሆናል፡፡ (በኢህአዴግ አድናቂ ማብዛት ያስገመግማላ!)
ግን እኮ ኢህአዴግ ብቻ ሳይሆን ደርግም ሆነ ጃንሆይ በአድናቂ ጉዳይ የተለዩ አይመስለኝም (አርፎ የሚገዛ እንጂ አድናቂ ምን ይረባል?) በእነ ምኒልክና አፄ ቴዎድሮስ ዘመን ግን የነበረውን አላውቅም፡፡ 
እኔ የምለው … እንዲያ ተሰልፈው ጠ/ሚኒስትሩን ሲያስፈርሙ ያየናቸው ምሁራን ከአንገታቸው ነው ከአንጀታቸው? (ሃቀኛና አስመሳይ አድናቂ ሊኖር ይችላል ብዬ እኮ ነው!) ከአንገትም ይሁን ከአንጀት ግን ጠ/ሚኒስትሩ በርካታ ምሁራንን አሰልፈው ፊርማቸውን በማኖር የመጀመሪያው የኢህአዴግ ከፍተኛ ሹም ይመስሉኛል፡፡ 
በነገራችን ላይ በዚያን ሰሞን በዚሁ ጋዜጣ “መልዕክቶቻችሁ” ዓምድ ላይ ስለጉዳዩ የወጣ አንድ ፅሁፍ፤ “አድናቆት ነው ማመልከቻ?” በሚል ምሁራኑን በነገር ሸንቆጥ ማድረጉን አስታውሳለሁ። ጠ/ሚኒስትሩ ግን በጋዜጣ ሳይሆን በፓርቲያቸው ተሸንቁጠው ሊሆን ይችላል፡፡ (ኢህአዴግ “ቀናተኛ” ነው አሉ!) የዩኒቨርሲቲ ምሁራንን ድባቅ ለመምታት ሄደው ድንገተኛ አድናቂዎች ማፍራታቸው እንዴት ላያስገመግም ይችላል? (“ከምሁራን ጋር መሞዳሞድ” ተብሎ ይሆናል?) 
ኢህአዴግ ግን ለምንድነው ለግለሰቦች ዕውቀትና ብቃት፣ ምጥቀትና ጥልቀት ዋጋ የማይሰጠው? (ለራሱ ሹማምንት ማለቴ እኮ ነው!) ራሳቸው ጠ/ሚኒስትሩ መወደስ የጀመሩት ካረፉ በኋላ እኮ ነው!! (ማድነቅ በህይወት እያሉ ይሻላል!)
በቅርቡ የኢህአዴግ ሹማምንት እርስ በርስ በተገማገሙ ወቅት የውጭ ጉዳይ ሚኒስትሩ ዶ/ር ቴዎድሮስ አድሃኖም ከፌስ ቡክ አጠቃቀማቸው ጋር በተያያዘ መገምገማቸወን በወሬ ወሬ ስሰማ (ግልፅ መረጃማ ከየት ይምጣ?!) በግርምት ተሞላሁ። (ሚኒስትሩ በማህበራዊ ሚዲያ “አክቲቭ” ናቸው!) እናላችሁ ግምገማው… “ፌስ ቡክን የራሱን ገጽታ ለመገንባት ይጠቀምበታል” የሚል ነበር አሉ፡፡ ክፋት አለው እንዴ!?) 
እሳቸውም ግን የዋዛ አይደሉም፡፡ በአግባቡ ተከላክለውና ተከራክረው መርታታቸውን ሰምቻለሁ፡፡ (ወንዳታ!) በነገራችን ላይ “የኢህአዴግ ደጋፊ ያልሆንኩ የዶ/ር ቴዎድሮስ አድሃኖም አድናቂ ነኝ” (ፊርማቸው ግን ይቀረኛል!) 
በነገራችሁ ላይ “ኢህአዴግን የማልቃወም የትግል ተወዳዳሪ ነኝ” የሚሉት የቀድሞ የፓርላማ አባል መጨረሻቸው እንዴት ሆነ? ይኸውላችሁ ሚኒስትሩ እኔ ብቻ ሳልሆን ብዙ ሺ አድናቂዎች አላቸው (በፌስ ቡክ ማለቴ ነው!) ሰሞኑን በሚሊኒየም አዳራሽ እየተከበረ ባለው “የዳያስፖራ ቀን” በዓል ላይ ደግሞ ከአንጋፋው ድምፃዊ አሊ ቢራ ጋር ተቃቅፈው አቀንቅነዋል (የአርቲስት ነፍስ ሳይኖራቸው አይቀርም!) 
ሚኒስትሩ ከመድረክ ከወረዱ በኋላም በአድናቂዎች ተከበውና ታጅበው ነበር፡፡ የአገር ዳያስፖራ እየተጋፋ ሲያስፈርማቸው ነበር አሉ። (አድናቆት ይሁን ማመልከቻ… አልተጣራም!) እግረመንገዴን አንድ ጥያቄ ብሰነዝርስ … አሁንም ዳያስፖራው “መሬት በነፃ” እና “መኪና ያለቀረጥ” የሚለውን ጥያቄ አልተወም የሚባለው እውነት ነው እንዴ? (እንድታዘባቸው ስለማልፈልግ እውነት ባልሆነ!)
ወደ ክቡር የውጭ ጉዳይ ሚኒስትሩ እንመለስ። ዶ/ር ቴዎድሮስ በሰሞኑ ተግባራቸው የግምገማ ቢላዋ እንደሚሳልላቸው የሚገመት ነው፡፡ (ልብ ያመነውን ፈጽሞ መገምገም ይሻላል!)
እናላችሁ … አንዳንዱ መድረክ ላይ ወጥተው፣ ማይክ ይዘው መዝፈናቸውን እንደሃጢያት ሊቆጥረው ይችላል፡፡ ሌላው እንደዝነኛ አርቲስት (Celebrity) ለዳያስፖራው መፈረማቸው ላይዋጥለት ይችላል፡፡ (“ከዳያስፖራ ጋር ተሞዳሞደ የሚልም አይጠፋም!) እውነቱ ግን ምን መሰላችሁ? ሚኒስትሩ ዘፈኑም … ፈረሙም… ሥራቸው ነው የሰሩት (የአሰራሩን መንገድ ግን ቀይረውታል!) ያልገባው ደግሞ ይጠይቃል እንጂ ለጭፍን ትችትስ አይነሳም፡፡ እንግዲህ “የዳያስፖራ ቀን” በዓልን ማዘጋጀት የእሳቸው መ/ቤት ሃላፊነት ይመስለኛል፡፡ እናም ዳያስፖራውን እንደ ሚኒስትር እላይ ተሰቅለው ሳይሆን እንደ አማካይ ሰው መሬት ወርደው ተቀበሉት፡፡ አስተናገዱት፡፡ ዘፈኑለት። ፈረሙለት፡፡ ይሄ ደግሞ ልብ ለልብ ያቀራርባል፡፡ ሰዋዊ ስሜትን ይፈጥራል፡፡ ተግባቦትን ያቀላጥፋል። የሥልጣን ግንብን ያፈርሳል፡፡ (ከዚህ በላይ ሥራ አለ እንዴ?)
በነገራችን ላይ እንኳንም አድናቂያቸው ሆንኩ ብያለሁ፡፡ አንድ ቀን ሲገጥሙኝ ደግሞ እንደ ምሁራኑ ወይም እንደ ዳያስፖራው ሳልጋፋ ቀስ ብዬ “ፈርሙልኝ” ማለቴ አይቀርም፡፡ (“አድናቆት ነው ማመልከቻ?” ከሚል ሽንቆጣ ለማምለጥ እኮ ነው!) እንደክቡር ሚኒስትሩ የፓርቲ ግምገማ ባይኖርብኝም የሰው ነቆራ ግን አይቀርልኝም፡፡ በዚህ አጋጣሚ በግሌ ዶ/ር ቴዎድሮስን “የዓመቱ ምርጥ ሚኒስትር” በሚል እንደመረጥኳቸው ለመግለፅ እወዳለሁ፡፡ (“የኢህአዴግ ደጋፊ ያልሆንኩ የሚኒስትሩ አድናቂ” መሆኔ እንዳይዘነጋ!) 
Source: Addis Admass

0 comments