Wednesday, August 19, 2015

ኢንጂነር ይልቃል ሰማያዊ ፓርቲን በድጋሚ ለመምራት ይወዳደራሉ

ሰማያዊ ፓርቲን ከምሥረታው ጀምሮ ላለፉት ሦስት ዓመታት በፕሬዚዳንትነት ሲመሩት የነበሩት ኢንጂነር ይልቃል ጌትነት፣ ፓርቲውን ዳግም ለመምራት ራሳቸውን ዕጩ ማድረጋቸውን አስታወቁ፡፡ፓርቲው ከተመሠረተ ወዲህ ለመጀመሪያ ጊዜ የሚያካሂደው ጠቅላላ ጉባዔ በመጪው ነሐሴ 16 እና 17 ቀን 2007 ዓ.ም.
የሚካሄድ ሲሆን፣ በወቅቱ በሚካሄደው የአዳዲስ አመራር ምርጫ ላይም በአሁኑ ጊዜ ፓርቲውን በፕሬዚዳንትነት እያገለገሉ የሚገኙት ኢንጂነር ይልቃል፣ ፓርቲውን ለቀጣዮቹ ሦስት ዓመታት በመሪነት ለማገልገል በዕጩነት እንደሚቀርቡ አረጋግጠዋል፡፡
በሰማያዊ ፓርቲ መተዳደርያ ደንብ መሠረት አንድ አባል ፓርቲውን ለመምራት ሁለት ጊዜ እንዲወዳደር ይፈቅዳል፡፡ ኢንጂነር ይልቃልም በዚህ ደንብ መሠረት ዳግም ፓርቲውን ለማገልገል እንደሚወዳደሩ ለሪፖርተር ገልጸዋል፡፡
ከዚህ በተጨማሪም ስለሚኖረው ውድድርና እነማን ተፎካካሪዎቻቸው ሊሆኑ እንደሚችሉ ለቀረበላቸው ጥያቄ፣ ‹‹እስካሁን ድረስ በግልጽ ራሱን ለፕሬዚዳንትነት ዕጩ አድርጐ ያቀረበ ተወዳዳሪ አባል የለም፡፡ እኔ ግን ለምክር ቤቱም ሆነ ለሚመለከታቸው አካላት ለፕሬዚዳንትነት እንደምወዳደር ይፋ አድርጌያለሁ፡፡ ተወዳዳሪዎች እንደሚኖሩ ጥርጥር የለውም፡፡ እስካሁን ይፋ ያደረገ ግን የለም፤›› ብለዋል፡፡
በፓርቲው መተዳደርያ ደንብ ላይ ጠቅላላ ጉባዔ በየአንድ ዓመቱ እንደሚሰበሰብ ይደነግጋል፡፡ ይሁንና እስካሁን ድረስ ጠቅላላ ጉባዔ ተጠርቶ አያውቅም፡፡ ያልጠራችሁት ለምንድነው ለሚለው ጥያቄ በሰጡት ምላሽ፣ ‹‹በየዓመቱ የሚለው እንደ ሁኔታው ነው የሚወሰነው፡፡ ፓርቲው በራሱ አስፈላጊ ነገሮች ሲኖሩና ጉባዔው ቢያያቸው ጥሩ ነው በሚል እሳቤ በየዓመቱ ጠቅላላ ጉባዔ ሊያካሂድ ይችላል እንጂ፣ በአስገዳጅነት በየዓመቱ መካሄድ አለበት የሚል ነገር የለም፡፡ በአስገዳጅነት መካሄድ አለበት የሚለው የሦስት ዓመቱ ነው፤›› ብለዋል፡፡ 
‹‹የጠቅላላ ጉባዔ ሥልጣን ትልቅ ነው ይባላል፡፡ ነገር ግን በተግባር ደረጃ ሲታይ ግን በሦስት ዓመት አንዴ ነው የሚሰበሰበው፡፡ ያንን ለምን አንቀይረውም በማለት በዚያ መሠረት ነው ደንባችን ውስጥ ያካተትነው እንጂ፣ የጠቅላላ ጉባዔው የሥልጣን ዘመን ለሦስት ዓመት ጊዜ ነው፤›› በማለት ጨምረው አስረድተዋል፡፡
የፓርቲው መተዳደርያ ደንብ የሥራ አስፈጻሚ ኮሚቴ ሥልጣንና ተግባር በሚመለከት የሚደነግገው አንቀጽ 13 ንዑስ አንቀጽ 13፣ ‹‹የሥራ አስፈጻሚ ኮሚቴ አባላት በድጋሚ ካልተመረጡ በስተቀር የሥራ ጊዜያቸው ሦስት ዓመት ይሆናል፡፡ በሊቀመንበርነት የኃላፊነት ቦታ ማገልገል የሚቻለው ለሁለት ተከታታይ ዙሮች ብቻ ነው፡፡ ሆኖም ከአንድ የሥራ ዘመን ዕረፍት በኋላ ተመልሶ ለዚያው ቦታ ሊመረጥ ይችላል፤›› ይላል፡፡ ይሁን እንጂ ጠቅላላ ጉባዔው መደበኛ ጉባዔውን በዓመት አንድ ጊዜ ማካሄድ እንዳለበት ደንቡ በአንቀጽ 24 ላይ ይደነግጋል፡፡ ከአቅም በላይ የሆነ ምክንያት ቢያጋጥምም ማራዘም የሚቻለው ለሦስት ወራት ብቻ እንደሆነ ያሰፍራል፡፡ ፕሬዚዳንቱ ያሉት አስገዳጅ የሆነ የጉባዔው ስብሰባ በየሦስት ዓመቱ እንደሆነ የሚገልጽ አንቀጽ ግን የለም፡፡ 
የፊታችን ቅዳሜና እሑድ በሚካሄደው የፓርቲው ጠቅላላ ጉባዔ በአጠቃላይ የነበረውን የፓርቲውን ጉዞ እንደሚገመገም የተገለጸ ሲሆን፣ በተጨማሪም ፓርቲው አሁን ካለበት ተነስቶ ምን ማድረግ አለበት የሚሉትን ጉዳዮች፣ እንዲሁም አጠቃላይ የአገሪቱንና የቀጣናውን የፖለቲካ ሁኔታ በመዳሰስ አቋም እንደሚወሰድ ፕሬዚዳንቱ አስታውቀዋል፡፡ 
በጠቅላላ ጉባዔው ለመሳተፍ ከመላው አገሪቱ የተውጣጡ 250 ያህል የፓርቲው አባላት እንደሚወከሉ ገልጸው፣ ‹‹ጠቅላላ ጉባዔውም ጠንካራ የትግል መንፈስ ለመፍጠርና ፓርቲው የነበሩትን ጠንካራና ደካማ ጐኖችን ገምግሞ፣ በጠንካራዎቹ ላይ የበለጠ ለመሥራት፣ ደካማ ጐኖችን ደግሞ እየቀረፈ በመሄድ ተጠናክሮ ለመሥራት አቅጣጫ ይቀመጣል፤›› በማለት ኢንጂነር ይልቃል የጠቅላላ ጉባዔው ውጤት ምን ሊሆን እንደሚችል ተናግረዋል፡፡
ሰማያዊ ፓርቲ በይፋ መመሥረቱን ያወጀው ታኅሳስ 2004 ዓ.ም. ላይ የነበረ ቢሆንም፣ በምሥረታው ወቅት ከብሔራዊ ምርጫ ቦርድ ጋር ውዝግብ ውስጥ መግባቱ የሚታወስ ነው፡፡ 
ፓርቲውንና ብሔራዊ ምርጫ ቦርድን አወዛግቦ የነበረው ጉዳይ ደግሞ ፓርቲው ያቀርበው የነበረ የሕግ አግባብ ነው፡፡ ይህም አንድ ፓርቲ የምሥረታ ጥያቄውን ለምርጫ ቦርድ ባቀረበ ሦስት ወራት ጊዜ ውስጥ ምላሽ ካልተሰጠው ዕውቅና እንደተሰጠው ይቆጠራል የሚለው ነው፡፡ በዚህም መሠረት ፓርቲው በታኅሳስ 2004 ዓ.ም. በሰጠው መግለጫ መመሥረቱን ይፋ ሲያደርግ፣ ከምርጫ ቦርድ ዕውቅና አግኝቶ መንቀሳቀስ የጀመረው ግን ከሐምሌ 3 ቀን 2004 ዓ.ም. ጀምሮ ነው፡፡
Source: Reporter

0 comments